Fana: At a Speed of Life!

48ኛው የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክርቤት መደበኛ ስብሰባ በካርቱም እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 48ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስት (ኢጋድ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በሱዳን ካርቱም መካሄድ ጀምሯል፡፡

በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢጋድ ዋና ፀሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ÷ ኢጋድ በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በቅርቡ በኢትዮጵያ የተደረሰው የሰላም ስምምነትም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዋና ፀሃፊው ኢጋድ ከዚህ በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን፣ ድርቅን እና ወቅታዊ የጎርፍ አደጋዎችን ለመከላከል እንዲሁም ለምግብ ዋስትና ያለውን ተግዳሮት ለመቅረፍ ምላሽ ለመስጠት ከአባል ሀገራት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

ስብሰባውን እየተካፈሉ የሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው÷ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ለቀጠናው ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት የኢጋድ አባል አገራት የሰጡት ያልተቋረጠ ድጋፍ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ምስጋና የሚያሰጠው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

በሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል የነበረውን ግጭት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊ ክብር ሙሉ በሙሉ ባከበረ መልኩ እንዲፈታ ከስምምነት መደረሱ በቀጠናው እና ከዚያም በላይ ላሉ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች ስለመኖራቸው ትምህርት ሰጪ አካሄድ መሆኑን አውስተዋል።

አቶ ደመቀ በአየር ንብረት ለውጥ እና እያደረሰ ባለው ተፅዕኖ ዙሪያ ያላቸውን ስጋት ገልጸው÷ይህን ለመፍታትም አባል ሀገራት እና አጋሮች የተቀናጀ ጥረት እንዲደረጉ መጠየቃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀጠናውን ሰላምና ደህንነት፣የሰብዓዊነት ሁኔታን ሪፖርት የሚያዳምጥ ሲሆን÷ በዛሬው እለትም ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.