Fana: At a Speed of Life!

በሶስት አቅጣጫ ወደ ትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ እየተጓጓዘ ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ለመድረስ ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር በሶስት አቅጣጫ (ኮሪደር) ወደ ትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ እያጓጓዘ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትና በህወሃት መካከል በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ መንግስት ቃል የገባውን በትግራይ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦትና የመልሶ ግንባታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛልም ነው ያለው።

ባለፉት አራት ቀናትም ዋና ዋና የሰብአዊ ድጋፍ በተለያየ አቅጣጫ እያቀረብ እንደሚገኝም ነው የገለጸው።

በዚህም በጎንደር ኮሪደር ሕዳር 17- ከጎንደር በሁመራ በኩል ወደ ሽረ 1 ሺህ 137 ሜትሪክ ቶን የምግብ እህል የጫኑ 30 የዓለም ምግብ ፕሮግራም የጭነት መኪኖች የተላኩ ሲሆን፥ በተጨማሪም 212 ሜትሪክ ቶን እህል የጫኑ 10 የጭነት መኪኖች ከጎንደር ወደ ማይፀብሪ መጓዛቸውንም አስታወቋል።

ከዚህ ባለፈም ሕዳር 18 ቀን የዓለም ምግብ ፕሮግራም በ24 መኪኖች 1 ሺህ 43 ሜትሪክ ቶን የምግብ እህል ከጎንደር ወደ ሽረ ሲላክ፥ ሕዳር 19 ቀን ከሽረ ወደ ማይፀብሪ የእርዳታ እህል የሚያጓጉዙ 11 ከባድ ተሽከርካሪዎች እየተጫኑ መሆኑንም ገልጿል።

ሕዳር 20 ቀን 380 ሜትሪክ ቶን የምግብ ድጋፍ የጫኑ 17 የዓለም ምግብ ፕሮግራም የጭነት መኪኖች ከጎንደር ወደ ማይፀብሪ (ዲማ) መላካቸውን በመጥቀስም፥ ከጎንደር ወደ ሽረ የምግብ ድጋፍ ያደረሱ 9 የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ጎንደር ተምለሰዋልም ነው ያለው።

እንዲሁም በኮምቦልቻ ኮሪደር ሕዳር 17 ቀን ከኮምቦልቻ የተነሱ 626 ሜትሪክ ቶን የምግብ ድጋፍን የጫኑ 22 የጭነት ተሽከርካሪዎች ዛታ የደረሱ ሲሆን፥ ሕዳር 18 ቀን የዓለም ምግብ ድርጅት 54 የምግብ እህል የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከኮምቦልቻ ተነስተው ወደ ኦፍላ፤ ራያ አላማጣ መድረሳቸውም ተገልጿል።

ሕዳር 19 ቀን በደቡባዊ ዞን ውስጥ ለሚገኙት ባላ፣ ኮረምና ሌሎችም ወረዳዎች የሚላክ የምግብ እህል ጭነት እየተካሄደ መሆኑንም ነው አገልግሎቱ የጠቀሰው።

በሰመራ ኮሪደርም ሕዳር 17 ቀን 34 የተለያየ ድጋፍ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መቐለ የደረሱ ሲሆን፥ 77 ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስ፣ 1 ሺህ 223 ሜትሪክ ቶን የምግብ እህል እንዲሁም 95 ሺህ 272 ሊትር ነዳጅ መቐለ ደርሰዋል ብሏል።

ሕዳር 18 ቀን በካቶሊክ ሪሊፍ ሰርቪስ በኩል የተላኩ በድምሩ 175 መኪኖች መቐለ ሲደርሱ፥ ሕዳር 20 ቀን የምግብ ድጋፍ የጫኑ 140 ተሽከርካሪዎች ከሰመራ ወደ መቐለ ጉዞ መጀመራቸውንም ነው ያስታወቀው።

ከዚህ በተጨማሪም ሕዳር 20 ቀን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ የአየር በረራ አገልግሎት በኩል ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ የመንገደኞች የአውሮፕላን በረራ መከናወኑንም በመግለጫው አመላክቷል።

ህዳር 21 ቀን 2015 ዓ.ም

 
አዲስ አበባ
 
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.