Fana: At a Speed of Life!

በተደረሰዉ የሠላም ስምምነት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል አንፃራዊ የሠላም ዓየር እየነፈሰ ነው – ዶክተር ለገሰ ቱሉ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተደረሰዉ የሠላም ስምምነት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል አንፃራዊ የሠላም ዓየር እየነፈሰ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሠ ቱሉ ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ÷ “በዓለማችን እንደ ሠላም የሚያስደስት ብሎም ለሰው ልጅ ተድላና መረጋጋትን የሚሠጥ ምንም ነገር የለም” ሲሉም ነው የሠላምን አይተኬነት ያመላከቱት፡፡

አያይዘውም አንዳንዶች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው እንኳ ምን እንደሚፈጠር እርግጠኛ ባልሆኑበት ሁኔታ ውስጣቸው ከተረጋጋ ሠላም አገኘሁ ይላሉም ብለዋል፡፡

እንዲህ ያለውን ” ውስጣዊ ሠላም” ም ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች እንዲተርፍ ይመኛሉ ነው ያሉት፡፡

“አንድ ሰው ሠላም አገኘ የሚባለው አዕምሮው ፀጥታ ሲያገኝና ሲረካ ነው” ሲሉም ሠላም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አውስተዋል፡፡

ውስጣዊ ሠላም ምን ያህል አዕምሮን እንደሚያሳርፍ ያመላከቱት ሚኒስትሩ፥ የሀገር ሠላምም እንዲሁ ነው ሲሉ ሁለቱን በማነጻጸር አቅርበዋል፡፡

የሀገር ሠላም ሲረጋገጥ ዜጎች በዙሪያቸው መረጋጋትና ፀጥታ መስፈኑን ሲያዩ እና ሲያገናዝቡ እፎይ ይላሉም ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

“የዛሬው የአክሱም ፅዮን፣ የኩሓ መቐለና የሌሎች አካባቢዎች ዓመታዊ የማሪያም ክብረ በዓል አከባበር ለዚህ ምስክር ነው” ሲሉ ነው የገለጹት፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች የነበረው የበዓል አካባበር እንደ ዱሮው እንኳ ባይሆንም የተጀመረው ሠላም ዳር እንዲደርስ በእጅጉ ተሥፋንና ደስታን የፈነጠቀ ነው ብለዋል፡፡

“በእጃችን የገባውን ሠላም መጠበቅና መንከባከብ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው” ሲሉም ስለ ሠላም ያላቸውን ሐሳብ አፅንዖት ሠጥተው አጠናክረዋል፡፡

“ዜጎች አጥብቀው የያዙት ሠላም ዘላቂ ይሆናል ፤ ሠላምን የሚጠሉ ኃይሎችም በቀላሉ አያደፈርሱትም” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

በሌሎች አካባቢዎች በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችም ባጠረ ጊዜ እንዲፈቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም በማኅበራዊ ትሥሥር ገፃቸው አመላክተዋል፡፡

መንግስት በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ ሠላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በቁርጠኝነት እየሠራ ነው ሲሉም ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ጠቁመዋል፡፡

ይህንን ጥረት ዘላቂ ለማድረግ ሠላም ወዳድ ኃይሎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በመደጋፍ መሥራት ይኖርባቸዋል ሲሉም አስገንዝበዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች እየደረሰ ያለው ጉዳትና ሕመም የሁላችንም ሕመምና ጉዳት ነዉ ሲሉም ነው ሁኔታውን የገለጹት፡፡

ችግሩን የብሔርና የአካባቢ ገፅታ ከመስጠት ይልቅ ለዘላቂና አዎንታዊ ሰላም አንድ ሆኖ በመቆም ለሰላማችን መረጋገጥ በጋራ መረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡

የሁሉም ወገኖች ዋስትና የሚኖሩትን ፍላጎቶችና ጥያቄዎች በሰላማዊ ውይይት መፍታት ብቻ ነው በማለትም ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ዉጭ ሌላው ኪሳራ ነው ፤ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለሚመጣ ሁሉ የመንግስት የሰላም በር ክፍት ነው ሲሉም አመላክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.