Fana: At a Speed of Life!

ሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በዝግጅት ላይ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም በመጀመሪያው ሪፎርም የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን ማጠናከርና የታዩ ተግዳሮቶችን መፍታት በሚያስችል መልኩ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስቴርና የገንዘብ ሚኒስቴር በሪፎርሙ ዝግጅት ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

በመጀመሪያው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የትግበራ ወቅት÷ በግብርና፣ በማዕድን፣ ቱሪዝም፣ በፋይናንስ ዘርፍ፣ በነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲሁም በተለያዩ የኢኮኖሚያዊ መስኮች ዕድገት መታየቱ ተገልጿል፡፡

የዋጋ ግሽበት፣ ኮቪድ 19 እና ሀገሪቱን ያጋጠማት ጦርነት እንዲሁም የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በተግዳሮትነት ተነስተዋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ ሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም የሚተገበረውን የሦስት ዓመታት የመንግስት የኢንቨስትመንት ዕቅድን ታሳቢ ማድረግ አለበት፡፡

ሪፎርሙ የመጀመሪያውን ማሻሻያ የፈተኑ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን በሚፈታ መልኩ እንዲዘጋጅም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በጋራ ይሠራል ነው ያሉት፡፡

ሪፎርሙ የማክሮ ፋይናንስና የሴክተር ቅንጅትን ታሳቢ ማድረግ አለበት ማለታቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር በሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ላይ ከሚኒስቴሮች ጋር ባደረገው ውይይት÷ በመጀመሪያው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አፈፃፀም የተመዘገቡ ውጤቶችን መቃኘትን ታሳቢ ያደረገና ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት በቀጣዩ ዕቅድ ሊካተቱና ትኩረት ሊደረግባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.