Fana: At a Speed of Life!

በቦሌ ክ/ከተማ ከ300 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቦሌ ክፍለ ከተማ ከ300 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በ90 ቀናት የሚተገበሩ የሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በተለያዩ የልማት ስራዎች ተጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነን ጨምሮ የከተማ፣ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች፣ ባለሀብቶችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የፕሮጀክቶቹ ግንባታ የማስጀመሪያ ስምምነት ሰነድ የመፈራረም ስነ-ስርዓትና የመሰረት ድንጋይም ተቀምጧል።

አቶ ጥራቱ በየነ በዚሁ ወቅት÷የሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ሁሉም ኢትዮጵያዊና የአዲስ አበባ ነዋሪ ጉልበቱን፣ እውቀቱንና  አቅሙን ተጠቅሞ በማስተባበር የተጀመሩ መልካም ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አለምጸሃይ ሽፈራው በበኩላቸው÷ግንባታቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች የቅድመ ሕጻናት ማዘውተሪያ ማዕከል፣ የዳቦና አትክልት መሸጫ ሱቆች ግንባታ፣ዘመናዊ የግብርና ማዕከል እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች የነዋሪውን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ለፕሮጀክቶች ተግባራዊነት  የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርም የወተት ልማት፣ የከብት ማድለብና የዶሮ እርባታ ነዋሪዎች እንዲያካሂዱ ስጦታ መበርከቱን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎንም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችና አቅመ ደካሞች የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር ተካሂዷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.