Fana: At a Speed of Life!

ዩ ኤን ዲ ፒ በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበበ፣ ሕዳር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩ ኤን ዲ ፒ) ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡
 
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ እና የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩ ኤን ዲ ፒ) የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት ÷ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጦርነት ፣ በኮቪድ- 19 ፣ በድርቅና በሌሎችም ከፍተኛ ውጫዊ ጫናዎች ቢፈተንም እድገት ማስመዝገብ ችሏል፡፡
 
እድገቱን መጠኑንና ፍጥነቱን ጨምሮ ለማስኬድም መንግስት የተለያዩ ስራዎችንና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
 
ለዚህም እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ያሉ የልማት አጋሮች ድጋፍ ይፈለጋል ብለዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ ካጋጠሟት ችግሮች ሁሉ በላይ ናት ያሉት ሚኒስትሯ÷ የልማት አጋሮችም የሀገሪቱ ዘላቂ ልማት በመደገፍ አጋርነታቸውን በማረጋገጥ ከመንግስት ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡
 
አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያሉባትን የኢኮኖሚ ችግሮች ለመቅረፍ በየጊዜው የተለያዩ የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን እያደረገች መሆኑን አንስተው÷ አሁንም 2ኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
የውጭ ምንዛሬ እጥረት ፣ የገቢና ወጪ ንግድ አለመመጣጠን ፣ የሸቀጦች ዋጋ መናር እና ሌሎች ችግሮችም ኢኮኖሚው ላይ መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
 
በሚደረገው ሪፎርም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ÷ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራምም ለዚህ ስኬታማ ስራ ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
 
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ሃላፊ አኪም ስታይን÷ በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መሃከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት ለኢትዮጵያ መንግስት ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡
 
በመልሶ ግንባታ ፣ ማቋቋምና እና በተለያዩ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ በሆኑ የልማት ስራዎች ላይ ድጋፋቸውን እንደሚጠናክሩ አስታውቀዋል፡፡
 
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጋር ቤተሰብ ነው ያሉት ኃላፊው÷ ይህ የልማት አጋርነት እየጎለበተ እንደሚሄድ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.