Fana: At a Speed of Life!

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 23 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ በሙስና ወይም ሌብነት ወንጀል የተጠረጠሩ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ አስታወቀ።
 
በቅርቡ የተቋቋመው የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ስራውን በይፋ መጀመሩን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል፡፡
 
ኮሚቴው በመግለጫው÷ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ በሙስና ወይም ሌብነት ወንጀል የተጠረጠሩ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።
 
በተጨማሪም በብሄራዊ ደህንነት አገልግሎት በተለያዩ የስራ ሃላፊነት ላይ ሲያገለግሉ የነበሩ የስራ ሃላፊዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተገልጿል፡፡
 
ግለሰቦቹ የተሰጣቸውን ሀላፊነት ያለአግባብ በመጠቀም ከግለሰቦች እና ከድርጅቶች ላይ ገንዘብ እና ንብረት ወስደዋል በሚል ተጠቁሞ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።
 
በአዲስ አበባም የአርሶ አደር ልጆች ያልሆኑ ልጆችን በማስመሰል ፣የልማት ተነሽ ሳይሆኑ በሀሰት ሙስና የሰሩ ግለሰቦች መለየታቸው ተመላክቷል፡፡
 
175 ሺህ ካሬ ቦታና የኮንዶሚንየም ቤት ምዝበራ የፈፀሙ እንዲሁም በፍትህ ዘርፉ ስልጣናቸውን በመጠቀም ከግለሰቦችና ከንግድ ተቋማት ጋር ሲሰሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ተለይተዋል ተብሏል።
 
ብሄራዊ ኮሚቴው በተቋቋመ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ከህብረተሰቡ ከ250 በላይ ጥቆማዎች መሰብሰባቸውም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
 
ህብረተሰቡ ሙሰኞችን በማጋለጡ ረገድ ጥቆማውን አጠናክሮ አንዲቀጥልም ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል።
 
በአዳነች አበበ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.