Fana: At a Speed of Life!

የግብር ከፋይ መለያ ቁጥርን ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር ለማስተሳሰር የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበበ፣ ሕዳር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር አሰጣጡን ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር ለማስተሳሰር ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በዛሬው ዕለት የስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ እና የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል ተፈራርመዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ስምምነቱ በግብር ከፋይ መለያ ቁጥር አሰጣጥ ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ እና ለግብር ከፋዮች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል፡፡

ተቋሙ ለግብር ከፋዮች የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ለመስጠት ለቴክኖሎጂ ግዥ የሚያወጣውን ወጪ በማስቀረትም የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ይረዳል ብለዋል፡፡

የግብር ከፋይ መለያ ቁጥርን ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር ማስተሳሰር ሀሰተኛ ማንነትን መሰረት በማድረግ የሚፈፀሙ ማጭበርበሮችንና ወንጀሎችን በቀላሉ ለመከላከል ስለሚረዳ የሀገርን ኢኮኖሚ እንዳይመዘበር ይረዳልም ነው ያሉት፡፡

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ ዘሚካኤል በበኩላቸው÷ የገቢዎች ሚኒስቴር ለሀገር አለኝታ የሆነውን ግብር የመሰብሰብ ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር በቅርቡ እንዲተሳሰር በማድረግ ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራ መግለጻቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.