Fana: At a Speed of Life!

የተደራጀ ሌብነትን ለመዋጋት የተቋቋመው የፀረ ሙስና ብሄራዊ ኮሚቴ ስራውን ጀመረ

አዲስ አበበ፣ ሕዳር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተደራጀ ሌብነትን ለመዋጋት የተቋቋመው የፀረ ሙስና ብሄራዊ ኮሚቴ ስራውን መጀመሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ብሄራዊ ኮሚቴው የመሬት እና የመንግስት ቤቶች አስተዳደር፣ የፀጥታና የፍትህ ዘርፍ፣ የፋይናንስ ዘርፍ፣ የመንግስት ገቢና ጉምሩክ ስርአት እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ፣ አስተዳደርና የመንግስት ግዢ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጓል።

ቀድሞ በተደረጉ ማጣራቶች በወንጀሉ የተጠረጠሩትን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ በብሄራዊ ደህንነት አገልግሎት ውስጥ በተለያየ ደረጃ ያሉ የስራ ሃላፊዎች፣ ፖሊስ፣ ዐቃቤ ህግና ዳኞች በቁጥጥር ስር ውለው ማጣራት እየተደረገባቸው ነው።

በወንጀሉ ተጠርጥረው ከሃገር የሸሹ ግለሰቦችንም ወደ ህግ ለማቅረብ ከተለያዩ ሃገራት ጋር ወንጀለኛን አሳልፎ የመስጠት ስምምነቶች ሲፈፀሙ መቆየታቸውንም አስታውሷል።

ብሄራዊ ኮሚቴው በተቋቋመ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ከህብረተሰቡ ከ250 በላይ ጥቆማዎች ተሰብስበዋል ያለው መግለጫው ህብረተሰቡ በ9555 ጥቆማውን እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።

በቀላልና በጥልቅ ማጣራት እርምጃ የሚወሰድባቸው ጥቆማዎች ተለይተዋል፤ በወንጀሉ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት የስራ ሃላፊዎች ላይ ክስ ይመሰረታል ነው የተባለው።

ብሄራዊ ኮሚቴው የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በተከታታይ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግም ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.