Fana: At a Speed of Life!

በዩኒቨርሲቲዎች መምህራንና ቴክኒካል ረዳቶች ስም የተሰራጨው አቋም ከማህበሩ እውቅና ውጭ መሆኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራንና ቴክኒካል ረዳቶች ስም የተሰራጨውን አቋም ማህበራችን አያውቀውም ሲል የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ለኢዜአ በላከው መግለጫ ማህበሩ ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምሀርት ድረስ መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎችን በማደራጀት በአምስት ዓላማዎች እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጿል።

ከአምስቱ ዓላማዎች መካከል አንዱ የመምህራን መብትና ጥቅም ማስከበር ነው ያለው መግለጫው፥ በአሁኑ ወቅት የዩኒቨርሲቲ መምህራን ያነሱትን ጥያቄዎች ለትምህርት ሚኒስቴርና ለሚመለክታቸው የፌዴራል መንግስት አካላት እያቀረበ ለመፍትሄው እየሰራ መሆኑንም አመልክቷል።

አንዳንድ ጥያቄዎች በፍጥነት ምላሽ ማግኘት የሚገባቸው መሆኑን ማህበሩ ቢያምንም አንዳንዶቹ ደግሞ ጊዜ የሚፈልጉ መሆናቸው ሊታወቅ እንደሚገባም አስታውቋል።

የመምህራን ማህበር የትግል ስልት መርህን መሰረት በማድረግ ለሌሎች አርዓያና ትምህርት ሰጪ በሆነ መልኩ መሆን እንዳለበትም የማህበሩ መግለጫ ያመለክታል።

ይህ በእንዲህ እያለ “የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራንና ቴክኒካል ረዳቶች የአቋም መግለጫ” በሚል ርዕስ “ከህዳር 26/2015 ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የሥራ ማቆም አድማ እናደርጋለን” በሚል ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨውን መረጃ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የማያውቀው ነው ብሏል።

እውቅና ያለው የማህበሩ መዋቅር ስምም “የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማህበር” መሆኑን ያስታወቀው መግለጫው መምህራንም ማህበራችሁ ጉዳዩን በጥብቅ ይዞ እየሰራ መሆኑን አውቃችሁ የተለመደውን የማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት በሙያዊ ኃላፊነታችሁን እንድትቀጥሉ ሲል ጥሪውን አስተላልፏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.