Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያገኘ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ÷ የሰላም ስምምነቱ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዳገኘና ለቀጣናው ሰላም መሆንም ጉልህ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።

የተለያዩ ሀገራትም ድጋፋቸውን እየገለጹ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የሱዳን ሉዓላዊ የሸግግር ምከር ቤት ፕሬዚዳንት ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት በመፈረሙ እንደተደሰቱ ገልጸዋል ነው ያሉት፡፡ አገራቸውም ለስምምነቱ አፈፃፀም ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል ነው የተባለው፡፡

እንዲሁም አሜሪካ ፣ የአውሮፓ ሕብረት ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ ኤስያ እና ፓስፊከ አካባቢ የሚገኙ በርካታ ሀገራት ለሰላም ስምምነቱ ያላቸውንድጋፍ በአምባሳደሮቻቸው በኩል መግለጻቸውን አምባሳደር መለስ ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን ማስተናገድ ጀምራለች ያሉት አምባሳደሩ÷ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ዓለም አቀፉ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባዔ ነው ብለዋል።

ጉባዔው በቀጣይ ለሚካሄዱ ሌሎች አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎች እንደ መንደርደሪያ ሆኖ የሚታይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2023 ከፍተኛ የሆነ የገጽታ ግንባታ እንደምታካሂድም በመግለጫው ተነስቷል።

ለዚህም በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችን ወደ ሀገር ውስጥ በመጥራት ስልጠና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በስልጠናውም የሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት ላይ መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን ማስገንዘብ፤ የዲፕሎማሲ ግንኙነታችንን ዳግም ወደ መደበኛ ግንኙነት እንዲመለስ የማለዘብ ስራ መስራት እና ወዳጅ ሀገራትን ማብዛት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ በዲፕሎማሲው መስክ የኢትዮጵያ ተጠቃሚነትን ለማስፋት ከሀገራዊ እና ዓለማ አቀፋዊ ሁኔታ ጋር በመቃኘት ለአምባሳደሮቹ ስልጠና እንደሚሰጥ ታውቋል።

በፈረንጆቹ አዲስ ዓመትም ዳያስፖራውን በማንቀሳቀስ ገቢ ማሰባሰብ፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ግኝትን ማስፋት፣ ለመልሶ ግንባታው የሚሆን ሀብት ማሰባሰብ እና ኢንቨስትመንት ፍሰት መሳብ ላይ ትኩረት ይደረጋል ተብሏል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.