Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት ለሚያደርገው የመልሶ ማቋቋም ሥራ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን- የተመድ የልማት ፕሮግራም

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተመድ የልማት ፕሮግራም በጦርነት የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም ኢትዮጵያ ለምታከናውነው ሥራ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ ገለጸ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ኃላፊ ኤቺም ስታይነር ጋር ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

አቶ ደመቀ በውይይቱ ላይ÷ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እና መንግስት የሰላም ስምምነቱ ተፈፃሚ እንዲሆን የያዘውን ቁርጠኛ አቋም አስረድተዋል፡፡

መንግስት የመልሶ ግንባት፣ ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ እና ተጠያቂነትን ማስፈን የሚሉትን ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ወደ ተግባር መግባቱንም አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሳለች እና ያልተገባ ጫና ሲደርስባት የልማት ድርጅቱ ላሳየው አጋርነት አመስግነዋል፡፡

በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት እና ህብረተሰቡን ለመደገፍ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን እና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎችም ያልተቋረጠ የሰብዓዊ ድጋፍ በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ትግራይ እየደረሰ ነው ብለዋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎችም የትምህርት፣ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮሙኒኬሽን እና ሌሎችም አገልግሎቶች ዳግም ጀምረዋል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የተመድ የልማት ፕሮግራም ድርጅት የመልሶ ማቋቋም ሥራን በማገዝ ከመንግሥት ጎን እንዲቆምም ጠይቀዋል፡፡

ኤቺም ስታይነር በበኩላቸው በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረውን ችግር በሰላም ስምምነት ለመቋጨት መንግሥት ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀው÷ በጦርነት የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም ድርጅታቸው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ሌሎች አጋር አካላትም በመልሶ ግንባታ ሂደት ላይ ትብብር እንዲያደርጉ በድርጅታቸው በኩል ሥራዎች እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.