Fana: At a Speed of Life!

“ሚሊየን ፈተናዎች፤ ሚሊየን ዕድሎች” በሚል መሪ ቃል የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ” ሚሊየን ፈተናዎች፤ ሚሊየን ዕድሎች” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንት ተካሄደ።
ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንት በዛሬው ዕለት ውሎ በፐብሊክ ኢንተርፕርነርሺፕ እና ዲጂታል ኢንተርፕርነርሺፕ ላይ የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡
አራተኛ ቀኑን በያዘው የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንት በቴክኖሎጂ ውድድር ፣ የጀማሪ ኢንተርፕራይዞች ውድድር ፣ አውደ ርዕይና ልምድ ልውውጥ፣ የቴክኒክ ሙያ እና የዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት አሰጣጥ እና በሌሎች መርሐ ግብሮች ተከብሯል፡፡
ፐብሊክ ኢንተርፕርነርሺፕ ቀዳሚው ውይይት እየተካሄደበት የሚገኝ ርዕሰ ጉዳይ ሲሆን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ያሉትን መልካም አሰራሮች ለማጎልበት እና እንቅፋት የሆኑትን ለመለወጥ ስለ ፐብሊክ አንተርፕርነርሺፕ መወያየት ጠቃሚ ነው ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ከውይይቱ የፐብሊክ (ህዝባዊ) ኢንተርፕርነርሺፕ ምንነትን በበቂ ደረጃ በማብራራት ለአሰራር ጠቃሚ የሆነ ውይይት ማድረግ እንደሚገባም ገልፀዋል።
ህዝባዊ ኢንተርፕርነርሺፕ ወደ ተግባር ለመቀየር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ያለመ እና አተገባበሩ ላይ የሚመክር የፓናል ውይይት በዘርፉ ላይ ልምድ ባካበቱ ባለሙያዎች መሪነት እየተደረገ ይገኛል።
ከተመሰረተ አጭር ጊዜን ያስቆጠረው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢንተርፕርነር አስተሳሰብን ባህል አድርጎ ለመገንባት በርካታ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው።
በተለይም መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የፐብሊክ ኢንተርፕርነርሺፕ አስተሳሰብን ባህል እንዲያደርጉ ለማስቻል ስልጠናዎችን ለተጠሪ ተቋማት እና የተለያዩ መንግስት መስሪያ ቤቶች እየሰጠ ይገኛል።
በመራኦል ከድር
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.