Fana: At a Speed of Life!

በኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ ንግድ ላይ የሚሳተፉ አካላት እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የውሳኔ ሐሳብ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ ንግድ ላይ የሚሳተፉ ሕገ-ወጦችን ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የውሳኔ ሐሳብ ይፋ አደረጉ።

የኮንትሮባንድ እና ሕገ ወጥ ንግድ መከላከል እና ቁጥጥርን አስመልክቶ የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በጋራ የሰጡት ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ሕገ-ወጥነት እና ሕገ-ወጦች ላይ ተከታታይ ሕጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ችግሩን ለመግታት እና የተሳለጠ የወጪ ንግድ ሥርዓት እንዲኖር በማድረግ የሀገራችንን ብልፅግና ለማረጋገጥ መንግሥት ልዩ ክትትል እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በዚህም መነሻነት በንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን መካከል በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቅ ውይይት ከተደረገ በኋላ የሚከተሉት ውሳኔዎች ተላልፈዋል።

1ኛ. ማንኛውም ግለሰብ፣ የንግድ ድርጅት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋም ወይም ኩባንያ የወጪ ንግድ ምርቶችን ይዞ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ምርቶቹ ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ መሆናቸውን እና የላኪውን ሕጋዊነት የሚያረጋግጥ የወጪ ንግድ የመላኪያ ፈቃድ (Export permit) እና ሌሎች ለወጪ ንግድ የሚጠየቁ ሰነዶችን ሳይይዝ እንዲሁም የምርት አስተሸሸግና ሌብሊንግ (Export packaging and product labelling)፣ ምርቱ ላይ ሳይኖር የጉምሩክ ኬላዎችን አቋርጦ ማለፍ በጥብቅ የተከለከለ ነው።

በመሆኑም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም የጭነት አገልግሎት ከመስጠታቸው በፊት እነኚሀን ሕጋዊ ዶክመንቶች በመጠየቅ አገልግሎት እንዲሰጡ ጥብቅ ማሳሳቢያ የተሰጠ ሲሆን ከላይ የተጠቀሱትን መስፈርቶች ሳያሟላ ወይም መሟላታቸውን ሳያረጋግጥ በጉምሩክ ኬላዎችም ይሁን ከኬላዎች ውጪ በሚደረጉ ፍተሻዎች ከተያዘ ወይም ማናቸውንም ሕጋዊ አሠራሮችን በማያከብሩ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል።

2ኛ. የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 55(2-ለ) ‘በክልሎች መካከል የሚኖር የንግድ ልውውጥ እንዲሁም የውጭ ንግድ ግንኙነትን በተመለከተ’ የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣን እና ተግባር መሆኑን በግልጽ ተደንግጓል። በዚሁ መሠረት የአስፈጻሚ አካላትን ተግባር እና ኃላፊነት ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 22 መሠረት በንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር ከሚሰጥ የወጪ ምርት መላኪያ ፍቃድ ውጪ በክልሎች አስፈፃሚ አካላት የሚሰጡ ፍቃዶች፣ መሸኛዎች እንዲሁም ሌሎች የይለፍ ማስረጃዎች ተቀባይነት የላቸውም ብቻ ሳይሆን ነጋዴዎችንም ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያደርጉ በመሆኑ የክልል አስፈፃሚ አካላት ከላይ የተገለጹትን ማስረጃዎች እንዳይሰጡ ውሳኔ ተላልፏል።

በመሆኑም ነጋዴዎች በክልል አስፈፃሚ አካላት የሚሰጡ ማስረጃዎችን አቅርበው መስተናገድ የማይችሉ ሲሆን ይህንን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽንን ተግባር ኃላፊነት እና አደረጃጀት ለመወሰን በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 437/2011 መሠረት ዕቃው የኮንትሮባንድ ዕቃ እንደሆነ ተቆጥሮ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አውቀው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ውሳኔ ተላልፏል።

3ኛ. የዚህን ሥራ አፈፃፀም ለመከታተል ከንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን እንዲሁም ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የኦፕሬሽን ቡድን በተቋቋመ ግብረ-ኃይል በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ተሰማርቶ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ተወስኗል።

ይህ ውሳኔ አገሪቱ ካሉባት ተደጋጋሚ ተግዳሮቶች በጽናት እየወጣች ወደ ከፍታዋ ማማ የምታደርገውን ጉዞ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያጠናክር መሆኑ ታውቆ ኅብረተሰቡ ወንጀለኞችን በማጋለጥ እንዲተባበር እና ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀርቧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.