Fana: At a Speed of Life!

በሕዝብ ጤናና ደኅንነት ላይ በተለያዩ መንገዶች ሽብር የሚነዙ አካላት ላይ የሕግ አስከባሪ አካላት ሕግ የማስከበር ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ታዘዋል- የጠ/ሚ ፅህፈት ቤት

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሁን ወቅት በሕዝብ ጤናና ደኅንነት ላይ በተለያዩ መንገዶች ሽብር የሚነዙ አካላት ላይ የሕግ አስከባሪ አካላት ሕግ የማስከበር ተግባራቸውን በጥብቅ እንዲያከናውኑ መታዘዛቸውንየጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
 
ፅህፈት ቤቱ በኢትዮጵያ ከተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የመረጃ አሰጣጥን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።
 
በመግለጫውም የጤና ቀውስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከሰት የተሳሳተ መረጃን ተቀብሎ ማሰራጨት ከቀውሱ እኩል ጎጂ ነው ብሏል።
 
ማንኛውም ዜጋ በእንደዚህ አይነት ወቅት የሐሰት ዜናዎችን ለማስቆም የሚችለውን ሁሉ ማድረግ እንዳለበት በመግለጫው አሳስቧል።
 
የፌደራል መንግሥት ኮቪድ19ን በተመለከተ በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት መረጃን የማደራጀት እና በየዕለቱ የማሠራጨት ሥራን እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክቷል።
 
ከዚህ በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣው ኮሚቴ እና ሌሎች ዐበይት ኮሚቴዎች ያላቸውን ወቅታዊ የሥራ ክንውን እያስተባበረ እና መረጃን እያስተላለፈ መሆኑን ገልጿል።
 
ፅህፈት ቤቱ ሕዝቡ እንዲህ ባለው አስከፊ ጊዜ የፓለቲካ ትርፍ ለማግኘት ከሚንቀሳቀሱ አካላት ነቅቶ ራሱን እንዲጠብቅ ጠይቋል።
 
የህብረተሰብ ጤና መረጃን ማዛባት እና በዜጎች መካከል ፍርሐት እና ረብሻን መንዛት በወንጀል የሚያስጠይቅ ሀገራዊ አንድነትን የሚያናጋ ተግባር ነው ብሏል።
 
በኮቪድ19 ላይ መረጃን የሚሰጡ ዐበይት አካላት የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት መሆናቸውን ፅህፈት ቤቱ አስታውቋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.