Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል “ከሞፈር ወደ ትራክተር” በሚል መሪ ቃል የሜካናይዜሽን የንቅናቄ መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በምርት ዘመኑ 716 ትራክተሮች በማሠራጨት ግብርናውን ወደ ሜካናይዜሽን ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ መታቀዱ ተገለጸ።

“ከሞፈር ወደ ትራክተር” በሚል መሪ ቃል የሜካናይዜሽን የንቅናቄ መድረክ በባህርዳር ከተማ እየተከናወነ ሲሆን በዚህ ወቅት እንደተገለጸው በ2015 የምርት ዘመን በክልሉ 716 ትራክተሮች እና 61 ኮምባይነሮች ለማሰራጨት ታቅዷል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው እንደተናገሩት ባለፈው የምርት ዘመን በክልሉ ከለማው 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር ውስጥ 10 ከመቶ የሚሆነው በሜካናይዜሽን ለምቷል።

ክልሉ 2 ሚሊየን ሄክታር በሜካናይዜሽን መልማት የሚችል ምቹ መሬት እንዳለው የተናገሩት አቶ አጀበ ይህን መሬት በሜካናይዜሽን ለማልማት ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዘንድሮ የሚሠራጩት ትራክተሮችም በክልሉ ያለውን የትራክተር ቁጥር ከ2 ሺህ 100 በላይ እንደሚያደርሰውም ነው የተናገሩት።

የክላስተር እርሻ መስፋፋት፣ በክልሉ መንግስትና በአርሶ አደሩ ያለው ፍላጎት እንዲሁም ተግባሩን ለመደገፍ የአበዳሪ ተቋማት ተነሳሽነት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ምክትል ቢሮ ሃላፊው ጠቁመዋል።

በበላይነህ ዘላለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.