Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 17ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን አከበረ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 17ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን “ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ ቃል አክብሯል ።

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በሥነ ስርዓቱ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ ሀገራችን የብዙ ማንነትና ብሔር ብሔረሰቦች ሀገር በመሆኗ በብዝኃነታችን ላይ የተመሠረተ አንድነታችን ለዘላቂ ሠላማችን ዋልታ ነው ብለዋል ።

የዘንድሮውን የኢትዮጵያ ብሔረ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ስናከብር በሰሜኑ ሀገራችን ክፍል የተከሰተውን ያልተገባ አውዳሚ ጦርነት በሰላም ለመፍታት ስምምነት ላይ በደረስንበት ወቅት መሆኑ በዓሉን ልዩና ውብ ያደርገዋል ብለዋል አፈ ጉባኤው።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር በበኩላቸው በአዲስ አበባ የዘንድሮው ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አከባበር ከወረዳዎች ጀምሮ ከሁሉም ህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በህብረ ብሔራዊ ስርዓቱ ዙሪያ በውይይት እየተከበረ መምጣቱን ገልፀዋል።

በዚህም ሥርዓቱን መሸከም የሚችል ተቋም ግንባታና በሥርዓቱ የእያንዳንዱ ዜጋ ምን አንደሆነ ግንዛቤ ተፈጥሯል ያሉት አፈ ጉባኤዋ፥ የህብረ ብሔራዊ አንድነት ሥርዓት ለዘላቂ ሰላም ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዝግጅቱ ላይ የከተማ አስተዳደሮች፣ የወረዳዎች አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ተወካዮች መገኘታቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.