Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢንዱስትሪ ልማት ምርጥ ፈጻሚ ከሆኑ 10 የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ ሆነች

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያን ከፈረንጆቹ 2019 እስከ 2021 በኢንዱስትሪ ልማት ምርጥ ፈጻሚ ከሆኑ 10 የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ አድርጎ አስፍሯታል፡፡
ባንኩ የአፍሪካ ሀገራት ከ2019 እስከ 2021 በኢንዱስትሪ ልማት ያስመዘገቡትን የዕድገት ደረጃ ከ2010 አንጻር በመመልከት አፈጻጸማቸውን በአሃዛዊ መረጃ በማስደገፍ ይፋ አድርጓል፡፡
በመረጃው በኢንዱስትሪ ልማት አፈጻጸም ከፍተኛ እመርታ በማሳየት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ቤኒን፣ ሞዛምቢክ፣ ሴኔጋል፣ ጊኒ፣ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ ፣ጋና እና ኡጋንዳ ተካተዋል፡፡
አንዳንድ ሀገራት በኢንዱስትሪ ዕድገታቸው ከፍተኛ ትኩረት ማግኘታቸውንም ነው መረጃው ያመላከተው፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ ቤኒን በፖሊሲ ደረጃ ስትራቴጂ ቀርጻ በካፒታል ኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ለኢንዱስትሪ ልማት ምቹ ምኅዳር በመፍጠር ዕድገት ማስመዝገቧን ለአብነት አንስቷል፡፡
ጂቡቲ፣ ኤርትራ እና ሞሪታኒያ ደግሞ ከፈረንጆቹ 2010 አንጻር በ2019፣ 2020 እና 2021 በማምረቻው ዘርፍ የተሻሉ እና ተወዳዳሪ የሆኑበትን ሦስት ዓመታት አሳልፈዋልም ነው ያለው፡፡
በኢንዱስትሪው ዘርፍ የጊኒ፣ ሴኔጋል፣ ጋቦን እና ሞዛምቢክ ኢኮኖሚም መሻሻል አሳይቷል ነው የተባለው።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ለአፍሪካ ዕድገት የኢንዱስትሪ ልማት መሠረታዊ መሆኑን እንደሚያምን ጠቁሟል፡፡
ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል፣ የአኅጉሪቱ የተፈጥሮ ፀጋ፣ በሀገራቱ በፍጥነት እያደገ ያለው ፍላጎት እና ገበያ ደግሞ በኢንዱስትሪ ልማት ላይ ትኩረት ላደረገው የአፍሪካ ኢኮኖሚ እንደ መስፈንጠሪያ የሚያገለግሉ ግብዓቶች እንደሆኑም ዘርዝሯል፡፡
የአፍሪካ ሀገራት በኢንዱስትሪው ዘርፍ በትኩረት ከሠሩ የአፍሪካ ኅብረት እስከ 2063 ዕውን ሊያደርግ ያስቀመጠውን ዘላቂ የልማት ግብ ስትራቴጂ ሊያሳካ እንደሚችልም በመረጃው ጠቅሷል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.