Fana: At a Speed of Life!

ለሚሰጠው አገልግሎት 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር እጅ መንሻ የጠየቀው ባለሙያ በቁጥጥር ሥር ዋለ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 24 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሚሰጠው መንግስታዊ አገልግሎት 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ጉቦ ጠይቆ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የተቀበለው ባለሙያ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን የአዲስ የአበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመሬት ሊዝ ባሙያ የሆነው አቶ ፋሲል አወቀ በቁጥጥር ስር የዋለው ኅዳር 23 ቀን 2015 ዓ.ም ነው፡፡

ባለሙያው የመኖሪያ ቤት ገዝቶ ካርታውን በስሙ ለማዛወር ከሄደ አገልግሎት ፈላጊ ግለሰብ ኃላፊነቱን ተገን አድርጎ “ቤቱ እግድ አለበት ፤ እግዱን አስነስቼ ነፃ ካርታ እሰጥሃለሁ” በማለት 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ጉቦ እንዲሰጠው መጠየቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ አመልክቷል፡፡

አገልግሎት ፈላጊውም 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብሩን በተጠርጣሪው የግል አካውንት ካስገባለት በኋላ ተጨማሪውን 2 ሚሊየን ብር እንዲያስገባለት ሲጠይቀው የግል ተበዳይ ጉዳዩን ለፖሊስ ማሳወቁ ነው የተመለከተው፡፡

ፖሊስም ተጠርጣሪውን ይዞ ምርመራው መቀጠሉን አስታውቋል፡፡

የግል ተበዳይ በተጠርጣሪው አካውንት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ገቢ ማድረጋቸው በምርመራ መረጋገጡን የአዲስ ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል፡፡

ኅብረተሰቡ ማንኛውንም የመንግስት አገልግሎት ለማግኘት በሚሄድበት ወቅት ጉቦ ሲጠየቅ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠት እንዳለበት ኮሚሽኑ መልዕክቱን አስተላፏል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.