Fana: At a Speed of Life!

ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች የነዳጅ ማደያዎችን ዳግም ወደ አገልግሎት ለመመለስ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ግጭት ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች የነዳጅ ማደያዎችን በአጭር ጊዜ ዳግም ወደ አገልግሎት ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ እንደገለጹት÷ ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚቀርበው ነዳጅ ሳይስተጓጎል ተደራሽ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር የነዳጅ ማደያዎች ተጠግነው ዳግም አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሠራ ነው፡፡

እስካሁን ባለው ሂደትም በሃራና ቆቦ አካባቢዎች በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ የማቅረቡ  ሥራ መጀመሩን ገልጸው÷ አላማጣ በሚገኙ ማደያዎች ከሚቀጥለው ሣምንት ጀምሮ ነዳጅ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።

በማይጸብሪ ፣ በአብዓላና አፍዴራ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ቶሎ ተጠግነው በቅርቡ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

እስከ ሽረ ያሉትን የነዳጅ ማደያዎች መረጃ የማጥራት ሥራ መከናወኑን ጠቁመው÷ በቀጣይ እስከ መቀሌ ያሉትን የነዳጅ ማደያዎች ፈትሾና ጉዳት የደረሰባቸውን ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት  ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል፡፡

እስከ ሽረ ያሉት አካባቢዎች በቀጣይ ሙሉ ለሙሉ ነዳጅ እንዲያገኙ የነዳጅ ታንከሮችንና የነዳጅ መቅጃዎችን መልሶ የመጠገን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.