Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል የሚከናወነው የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭት ተጠናክሮ ቀጥሏል – ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የሚከናወነው የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭት ተጠናክሮ መቀጠሉን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በዚህ መሰረትም ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ 78 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እቃዎች በመንግስት እና በአጋር አካላት በትግራይ ክልል ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች መሰራጨታቸው ተገልጿል፡፡

እስከ ህዳር 23 ቀን 2015 ዓ.ም  ድረስም 72 ሺህ 160 ነጥብ 8 ሜትሪክ ቶን ምግብ እና አልሚ ምግብ በክልሉ መሰራጨቱን ኮሚሽኑ በተለይ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስታውቋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 13 ሺህ 686 ነጥብ 8 ሜትሪክ ቶን ምግብ፣1 ሺህ 13 ነጥብ 76 ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕቃዎች  እና 575 ሺህ 908 ሊትር ነዳጅ በመንግስት የተጓጓዘ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

መንግስት በተለይም አጋር አካላት መድረስ በማይችሉባቸው አካባቢዎች ላይ አስፈላጊውን የሰብዓዊ እርዳታ እያሰራጨ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

እስከ ተጠቀሰው ጊዜም በመንግስት እና አጋር አካላት 78 ሺህ 742 ነጥብ 16 ሜትሪክ ቶን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ የእርዳታ ቁሳቁስ መሰራጨቱ ነው የተገለጸው፡፡

የሰብዓዊ እርዳታውን በማሰራጨቱ ሒደት ከመንግስት በተጨማሪ 23 አጋር አካላት መሳተፋቸውን ኮሚሽኑ ጠቁሟል፡፡

ለሰብዓዊ እርዳታው ማጓጓዣም በአፋር-አብአላ፣በጎንደር-ማይጠብሪ-ሽረ እና በኮምቦልቻ-ቆቦ-አላማጣ ኮሪዶሮችን መጠቀም መቻሉ ተገልጿል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.