Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አንድነት የመኪና ማቆሚያ ፕሮጀክትን መረቁ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አንድነት የመኪና ማቆሚያ ፕሮጄክትን መረቁ፡፡
 
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዲሁም የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በአዲስ አበባ እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጄክቶች ትናትን፣ ዛሬን እና ነገን የሚያገናኙ ናቸው ብለዋል፡፡
 
ለሚቀጥለው ትውልድ የሚመጥን ስራ እያጠናቀቅን የነገይቱን ኢትዮጵያ ምስል እያየን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
 
ከመስቀል አደባባይ እስከ እንጦጦ፣ ከአብርሆት ቤተ መጽሐፍ እስከ ሳይንስ ሙዚዬም፣ ከአንድነት ፓርክ እስከ ወዳጅነት ፓርክ ያሉ ፕሮጀክቶች የትናንት ትውስታችንን የዛሬ ምልከታችንና የነገ መዳረሻችንን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
 
ሁሉም ስራዎች ለኢትዮጵያ የሚገባትን ብልጽግና የሚያመጡ መሆናቸውንም ነው ያወሱት፡፡
 
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1 ጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባው አንድነት የመኪና ማቆሚያ ፕሮጄክት በ9 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
ፕሮጄክቱ መጀመሪያ ወለል ላይና ከታች ባሉ አራት ተከታታይ የምድር ወለሎች አውቶቡሶችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ1 ሺህ 20 በላይ ተሸከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ እንደሚችል ተመላክቷል፡፡
 
በተጨማሪም አምፊ ቴዓትር፣ ባሕላዊ ምግብ ቤቶች፣ ሱቆችና ሌሎች መዝናኛዎችን ያካተተ መሆኑ ነው የተጠቆመው፡፡
 
ከዚህ ባለፈም ሕንጻው በመሬት ውስጥ ዋሻ ከአንድነት ፓርክ ጋር የተገናኘ በመሆኑ ፓርኩን ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻነት ክብር እንደሚያጎናጽፈው ተገልጿል፡፡
 
ዛሬ ለአገልግሎት በይፋ የተከፈተው አንድነት የመኪና ማቆሚያ ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥና ታሪካዊ ገፅታውን ሳይለቅ ለትውልድ እንዲተላለፍ ሆኖ የተሰራ ነው ተብሏል፡፡
 
የመኪና ማቆሚያ ሕንጻው ከመስቀል አደባባይ አንስቶ እስከ አብርሆት ቤተ መጽሀፍት ላሉት የብሔራዊ ቤተመንግሥት፣ ሳይንስ ሙዝዬም፣ ወዳጅነት አደባባይ ምዕራፍ አንድ፣ ወዳጅነት አደባባይ ምዕራፍ ሁለት እና ለሌሎችም መሰል ሰው ተኮር ልማት መዳረሻዎች የጉብኘት ቀለበት አንድ ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል ተጠቁሟል፡፡
 
ለአንድ የመኪና ማቆሚያ ከ200 በላይ ካሜራዎች የተገጠሙ ሲሆን÷ ካሜራዎቹ መኪና የቆመበትን ጊዜ ከመቁጠር ባለፈ ደህንነቱ የተጠበቀ የመኪና ማቆሚያን የሚያረጋግጥ ክትትል እና የመኪናው መለያ ሰሌዳ እንዲሁም የተገልጋዩን ማንነት ይለያሉ፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.