Fana: At a Speed of Life!

17ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል- የሲዳማ ክልል

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እን ሕዝቦች ቀን ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ እንደገለጹት÷የፊታችን ህዳር 29 በሀዋሳ ከተማ የሚከበረው 17ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ምክንያት በማድረግ ሊከሰት የሚችልን ስጋት ነፃ ለማድረግ እና በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

ቀኑ ሰላማዊና ህብረብሄራዊ አንድነት የሚታይበት በዓል እንዲሆን የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ሃይል፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና  የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ በቅንጅት አንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ በዓሉ በሰላም እንዲከበር የፀጥታ ሃይሉ ዝግጅት ብቻ በቂ አለመሆኑን ጠቁመው÷ ማህበረሰቡ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የከተማው ወጣቶች በበኩላቸው÷ በበዓሉ  ሀዋሳ ከተማ የፍቅር ከተማ መሆኗን ለማሳየት፣ እንግዶችን መንገድ ከማሳየት ጀምሮ ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ከፀጥታ አካላት ጋር ሆነን እንሰራለን ብለዋል።

በተለይ በበዓሉ ወጣቶችን የማይገልፁ እንቅስቃሴን ሊያደርጉ የሚችሉትን በመለየት የበኩላችንን እንወጣለን ነው ያሉት፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ  የጸጥታ ኃይሎች እና ወጣቶች በዛሬው ዕለት የእግር ጉዞ አድርገዋል።

 

በጥላሁን ይልማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.