Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 4 ወራት ቡናን ወደ ውጭ በመላክ 526 ሚሊየን ዶላር ተገኝቷል – ባለስልጣኑ

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አራት ወራት ቡናን ወደ ውጭ በመላክ 526 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ኮሎምቢያና ስፔንን ጨምሮ ከተለያዩ ቡና አምራች ሀገራት ባለሙያዎች ጋር በአዲስ አበባ እየመከረ ነው።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በመድረኩ የበጀት ዓመቱን አራት ወራት የኢትዮጵያን የቡና ምርት ግብይት በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል።

ባለስልጣኑ በበጀት ዓመቱ ቡናን ወደ ውጭ በመላክ 2 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታውሰው÷ ባለፉት አራት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ምርት 526 ሚሊየን ዶላር ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት 810 ሺህ ቶን የቡና ምርትን ወደ ውጭ በመላክ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት እንደታቀደ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የእስካሁኑ እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

በበጀት ዓመቱ የተቀመጠውን ዕቅድ ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር አዱኛ÷የዘንድሮው የአራት ወራት አፈጻጸም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ126 ሚሊየን ዶላር ብልጫ እንዳለውም አንስተዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.