Fana: At a Speed of Life!

የባለሞተር ተሽከርካሪ ነጋዴዎችን እንደ ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የተሰየሙ የንግድና የሙያ ስራዎች መሰያሚያ መመሪያ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የባለሞተር ተሽከርካሪ ነጋዴዎችን እንደ ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የተሰየሙ የንግድና የሙያ ስራዎች መሰያሚያ መመሪያ ቁጥር 934/2015 መዘጋጀቱን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡

መመሪያው የተዘጋጀው በወንጀል የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንዲቻል በአዋጅ ቁጥር 780/2005 መሰረት ሃላፊነት የተሰጣቸው የባለድርሻ አካላት በሚያከናውኑት ተግባር ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን አሰራር ለመፍጠር ነው ተብሏል፡፡

የባለሞተር ተሽከርካሪ ነጋዴዎችን እንደ ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የተሰየሙ የንግድና የሙያ ስራዎች መሰየም ያስፈለገበት ምክንያት የባለሞተር ተሽከርካሪዎች የንግድ ስርዓት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል መደበቂያ ዘርፍ መሆናቸው በጥናት የተረጋገጠ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በመሆኑም መመሪያው የባለሞተር ተሽከርካሪዎች ነጋዴዎችን ወንጀሎቹን ከመከላከል አኳያ ኃላፊነታቸውን በህግ ማዕቀፍ በማስቀመጥ የወንጀሎቹ መፈጸሚያ መሳሪያ እንዳይሆኑ ለመጠበቅ እና ወንጀሎቹ በእነሱ አማካኝነት እንዳይፈጸም ለመከላከል መሆኑ ተገልጿል፡፡

የባለሞተር ተሽከርካሪ ነጋዴዎች የሞተር ተሽከርካሪዎችን የሚያመርቱ፣ ከውጪ ሀገርፍ የሚያስመጡ፣ ወደ ውጪ ሀገራት የሚልኩ፣ የሚያከፋፍሉ፣ የሚያከራዩ፣ ለሽያጭ የሚደልሉ እና ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት እንደሚያጠቃልል ተጠቁሟል፡፡

በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ 780/2005 መሰረት በዚህ መመሪያ ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የተሰየሙ የንግድና የሙያ ስራዎች ተብለው ተሰይመዋል፡፡

በመመሪያው መሰረት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የባለሞተር ተሸከርካሪ ነጋዴዎች የውስጥ ፖሊሲዎችንና የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት፣ ወንጀሎችን ለመለየትና ለመፈተሽ የስጋት ዳሰሳ ጥናት ማድረግ፣ ደንበኞቻቸው የሚደቅኑትን ስጋት ለመለየት እንደሚያስችላቸው ተጠቅሷል፡፡

ለዚህም ከደንበኞቻቸው አስፈላጊ መረጃዎችን መቀበልና የተጠናከሩ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ፣ ከፍተኛ ስጋት ያለባቸውን ደንበኞች መለየት እና በሚደረገው የግብይት ሂደት ጥርጣሬ ወይም ለመጠርጠር ምክንያታዊ መሰረት ሲኖር ግብይቱን ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ወዲያውኑ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለባቸው የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህ መመሪያ መሰረት ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የተሰየሙ የንግድና የሙያ ስራዎች ውስጥ የተሰየሙት የባለሞተር ተሽከርካሪ ነጋዴዎች ይህንን መመሪያ የሚጥሱ ከሆነ የባለሞተር ተሽከርካሪ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር፣ ለመከታተል እና ፍቃድ ለመስጠት አግባብነት ባላቸው ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች በሚጣሉ አስተዳደራዊ ቅጣቶች ተጠያቂ ይሆናሉ መባሉን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 ላይ እንደተደነገገው ወንጀሎቹን ለመከላከል ሀላፊነት እና ተጠያቂነት ከተጣለባቸው የባለድርሻ አካላት መካከል የተለያዩ የንግድና የሙያ ስራዎች የሚያከናውኑ አካላት “ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ የተሰየሙ የንግድና የሙያ ስራዎች” በሚለው መጠቃለላቸው ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.