Fana: At a Speed of Life!

የሶማሌ ክልል የሙስና ተጋላጭ የሆኑ የግልና የጋራ ንብረቶች ለሌላ ወገን እንዳይተላለፉ በጊዜያዊነት አገደ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል በቅርቡ የተቋቋመው ክልላዊ የፀረ-ሙስና ኮሚቴ የግልና የጋራ ንብረት ለሌላ ወገን እንዳይተላለፉ በጊዜያዊነት ማገዱን አስታውቋል፡፡

የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚቴ ተልዕኮውን ለመወጣት እንቅፋት ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮችን አስመልከቶ የመጀመሪያ ሰብሰባውን በማካሄድ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ኮሚቴው በመግለጫው÷በክልሉ ሙስናን ለመከላከልና ከዚህ ጋር ተያያዥ ጉዳዮችን በጥልቀት ለመመርመር የሚረዱ ንዑስ ኮሚቴ ለማቋቋም ስለሚቻልበት ሁኔታ መምከሩን አንስቷል፡፡

በዚህም÷ በክልሉ የሙስና ተግባራት ላይ ክትትልና ምርመራ በማድረግ የሙስና ተጋላጭ የሆኑና ከንብረት ጋር በተያያዘ በጊዜያዊነት ማገዱን አስታውቋል።

እግዱ ከትናንት ጀምሮ ለሶስት ወራት የሚቆይ ሲሆን÷ ይህም የግል ቤት ካርታ፣ የመሬት ይዞታና ተሽከርካሪዎች ለሌላ ወገን እንዳይተላለፉ የሚከለክል መሆኑን ተመላክቷል።

እግዱ በሙስና የተጠረጠሩ የመንግስትና የህዝብ ንብረት ለተወሰነ ጊዜ ለመመርመር ብሎም በሙስና የተገኘ ንብረት ማሸሽ እንዳይቻል ለማድረግ ያለመ መሆኑ በመግለጫው ተጠቁሟል።

ኮሚቴው የወጣው የእግድ ትዕዛዝ ለንግድና ትራንስፖርት ቢሮ፣ ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ፣ ለከተማ አስተዳደሮች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንዲደርስ እንደሚደረግ መግለጹንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.