Fana: At a Speed of Life!

ጃፓን በኢትዮጵያ በድርቅና ግጭት ለተጎዱ ወገኖች 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የሰብዓዊ ድጋፍ ልታደርግ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጃፓን መንግሥት በኢትዮጵያ በድርቅና ግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የሚያወጣ ሰብዓዊ ድጋፍ ሊያቀርብ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ መረጃ እንዳለመላከተው ድጋፉ ÷ በአማራ ፣ አፋር ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ ትግራይ እና ሶማሌ ክልሎች በሚገኙ የጉዳቱ ተጋላጭ ወገኖች የሚሰጥ ነው፡፡

የምግብ ዋስትናና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ፣ እናቶችን እና ሴቶችን በሥርዓተ ፆታና ሥነተዋልዶ በኩል በመድረስ የጤና ክትትል እና ድጋፍ ለማድረስ ፣ ለሕፃናት አልሚ ምግብ ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም የእንስሳት ክሊኒኮችን በማቋቋም የእንስሳት ክትባቶችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ ተመላክቷል፡፡

በክልሎቹ በተከሰተው ግጭትና ድርቅ ምክንያት ለተፈናቀሉ እና ወደቀያቸው ለተመለሱ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፉ ተደራሽ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

ጃፓን ድጋፉን የምታቀርበው በምግብ ፕሮግራም፣ በምግብ እና እርሻ ድርጅት ፣ በፍልሠተኞች ድርጅት ፣ በቀይ መስቀል ኮሚቴ እንዲሁም በተመድ የሥደተኞች ኤጀንሲ ፣ በዓለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅት፣ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ እንዲሁም በሌሎችም ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች በኩል መሆኑን አስታውቃለች፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.