Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ እና በክልሎች ከአመራሮች ጋር በመመሳጠር ከፍተኛ መሬት በህገ ወጥ መንገድ ለግለሰቦች እንዲሰጥ አድርገዋል የተባሉ ከ23 በላይ የመሬት ደላላዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ እና በክልሎች ከተለያዩ አመራሮች፣ ባለሙያዎች ጋር በመመሳጠር አንዲሁም ለባለስልጣን ሽፋን በመሆን ከፍተኛ መሬት በህገ ወጥ መንገድ ለግለሰቦች እንዲሰጥ አድረገዋል ተብለው የተጠረጠሩ ከ23 በላይ ህገ ወጥ የመሬት ደላላዎች በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቀረቡ።
ተጠርጣሪዎቹ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ሁለተኛ የወንጀል ችሎት ነው በዛሬው ዕለት የቀረቡት።
ተጠርጣሪዎቹ በክልሎችና አዲስ አበባ ከሚገኙ በተለያየ ደረጃ ያሉ የስራ ሃላፊዎች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር ካርታ በህገ ወጥ መንገድ በማስወጣት ለግለሰቦች እንዲተላለፍ ማድረጋቸውን መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ በተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቂያው አቅርቧል።
በተለይም ከአርሶ አደር ኮሚቴዎች ጋር በመገናኝትና ሀሰተኛ ማስረጃ እንዲያቀርቡ በማድረግ ብዙ ሺህ ካሬ ሜትር ከመሬት ባንክ ውስጥ ወጥቶ ለግለሰቦች እንዲደርስ ማድረጋቸውም ተጠቅሷል።
በተጨማሪም የይገባኛል ጥያቄ ተነሰቶባቸው በክርክር ላይ የሚገኙ ቦታዎችን በማጠር ባላቸው ግንኙነት ሐሰተኛ ሰነድ በማቅረብ ጭምር መጠርጠራቸውም ተገልጿል።
የተገኘውንም መሬት ለራሳቸው የወሰዱ በመሆኑ እና ለስራ ሃላፊዎች ሽፋን በመስጠት እንዲወስዱ በማድረግ በህገ ወጥ ድርጊታቸው የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ከፍተኛ ሃብት ያካበቱ በመሆኑ በህገ ወጥ የድለላ ስራ ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው በምርመራ ከህዳር 23 እስከ 25 ቀን 2015ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው የተባለው፡፡
የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮም የምስክሮችን ቃል በመቀበል፣ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ሰነዶችን በማሰባሰብ እና ከተለያዩ ባንኮች የሂሳብ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል።
በበላይ ተስፋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.