Fana: At a Speed of Life!

በውጭና በሀገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአማራ ክልል የሚከናወኑ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን እንዲያግዙ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የሚከናወኑ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን በውጭ እና በሀገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲደግፉ በክልሉ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ጥሪ አቀረበ፡፡
ከሰኔ 2013 እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም ድረስ በነበረው ግጭት በአማራ ክልል 292 ቢሊየን ብር ኪሳራ መድረሱ ተገልጿል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አባተ ጌታሁን ለፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ የአምስት ዓመት ዕቅድ ተዘጋጅቶ በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ የሚመለሱ ጉዳዮች ተለይተው እየተሠራ ነው፡፡

ቅድሚያ ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ ለተለዩ ዘጠኝ ዘርፎች 1 ቢሊየን 129 ሚሊየን ብር ተመድቦ የመልሶ ማቋቋም ግንባታ መርሐ ግብር ተጀምሯል ነው ያሉት፡፡

በዚህም 3 ሺህ መኖሪያ ቤቶች፣ 22 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 10 የጤና ተቋማት፣ 31 የንጹሕ ውኃ መጠጥ አውታሮች፣ 10 የሥራና ስልጠና ማዕከላት፣ 65 የግብርና ፕሮጀክቶች፣ 10 የመስኖ አውታሮች፣ 17 የወጣቶች ሰብዕና መገንቢያ ማዕከላት፣ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን 2 ሺህ 102 ሴቶች ተደራሽ የሚያደርግ የመልሶ ማቋቋም ሥራ በአራት ወራት ውስጥ ይከናወናል ብለዋል፡፡

ዘጠኙ ዘርፎች በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ጎንደር እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች እንዲሁም ደሴ፣ ኮምቦልቻ እና ወልዲያ ከተሞች እንደሚከናወኑ ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ክልል በተደራጀ ሁኔታ በራያ ቆቦ ወረዳ ወርቄና ያያ (023 እና 024) ቀበሌዎች የመልሶ ማቋቋም ሥራ መጀመሩን አስታውሰው፥ በዚህም በአራት ወራት የሚጠናቀቁ 234 ቤቶች፣ አንድ ትምህርት ቤት፣ አንድ ጤና ጣቢያ እና አንድ የእንስሳት ክሊኒክ ግንባታ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

ከፌዴራል መንግሥት እና ከዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች በሚገኝ ድጋፍ እንዲሁም የክልሉን ሕዝብ ያሳተፈ የድጋፍ ንቅናቄ በማካሔድ ሁለተኛው ዙር የመልሶ ማቋቋም ሥራ በቅርቡ እንደሚጀመርም ዋና ሥራ አስኪያጁ አመላክተዋል፡፡

ይህን የመልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ሥራ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲደግፉ ነው ኃላፊው ጥሪ ያቀረቡት።

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.