Fana: At a Speed of Life!

የሁለት ልጆቿን አባት በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለችው ግለሰብ በ21 ዓመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የሁለት ልጆቿን አባትና ባለቤቷን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለችው ግለሰብ በ21 ዓመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ ተወሰነባት፡፡

በተመሳሳይ ከባድ የውንብድና ወንጀል በመፈፀም የሰው ሕይወት ያጠፉ ሁለት ግለሰቦች በ18 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጥተዋል፡፡

ተከሳሽ ከበቡሽ ዓለሙ የሁለት ልጆቿን አባት ሕይወት እንዲያልፍ ያደረገችው መጋቢት 14 ቀን 2014 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው 58 መዝናኛ ጀርባ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡

“በተደጋጋሚ ይሰድበኛል” በሚል በባለቤቷ ላይ ቂም የያዘችው ተከሳሽ÷ ባለቤቷ በእንቅልፍ ላይ ሳለ ደጋግማ በመጥረቢያ በመምታት ሕይወቱ እንዲያልፍ ማድረጓን የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል፡፡

ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ የከባድ ውንብድና እና ግድያ ወንጀል ችሎት በ21 ዓመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ ወስኗል፡፡

በተመሳሳይ ኢያሱ ኤርዶ እና ማሙሽ ቶማስ የተባሉ ግለሰቦች÷ ሚያዚያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ30 ገደማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ሱቄ ማርያም አካባቢ በፈፀሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል ጥፋተኝነታቸው በመረጋገጡ በፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል፡፡

ተከሳሾቹ ሞገስ ሞታ የተባለውን ግለሰብ ደጋግመው በመደብደብ ሕይወቱ እንዲያልፍ ካደረጉ በኋላም የእጅ ስልኩን እና የለበሰውን ልብስ አውልቀው መውሰዳቸው ተገልጿል፡፡

ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ የከባድ ውንብድና እና ግድያ ወንጀል ችሎት እያንዳንዳቸው በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.