Fana: At a Speed of Life!

በኢኮኖሚ ዘርፍ የሚፈጸሙ አሻጥሮችና የሙስና ድርጊቶችን ለመከላከል ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት በኢኮኖሚ ዘርፍ የሚፈጸሙ አሻጥሮችና የሙስናን ድርጊቶችን ለመከላከል ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ሲሉ የብሔራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተሩ ጀነራል ሲሳይ ቶላ ገልጸዋል፡፡

በብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሥር የሚገኘው ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኢኮኖሚ ደኅንነት እና በጉምሩክ ኮሚሽን የሕግ ማስከበር መረጃ ኪነሙያ ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች አስመርቋል፡፡

የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ በኢኮኖሚ ዘርፍ የሚፈጸሙ አሻጥሮችና የሙስናን ድርጊቶችን ለመከላከል ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡

በዚህ ወቅት ለመመረቅ የበቁት ሰልጣኞችም በሚሰማሩበት መስክ ሀገርንና ሕዝብን በማስቀደም በጥብቅ ሙያዊ ስነምግባር የሚሰጠቸውን ስምሪት በብቃት መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡

ስልጠናው ለኢኮኖሚ ደኅንነት ጀማሪ የመረጃ ኦፊሰሮችና ለጉምሩክ ኮሚሽን የሕግ ማስከበር መረጃ ኦፊሰሮች መሰጠቱን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጉሙሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ በየነ በበኩላቸው÷ ኮሚሽኑ ያለበትን ብቁ የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር ለመቅረፍ ከብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጋር በጥምረት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.