Fana: At a Speed of Life!

በምግብ ራስን መቻል የህዝብን መሰረታዊ ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ የሀገርን ክብርም ማስጠበቅ ነው-ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በምግብ ራሳችንን ከቻልን የህዝባችንን መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት ብቻ ሳይሆን የሀገርን ክብርም የምናስጠብቅበት ይሆናል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ግብርናን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እስካሁን በተደረጉ ጥረቶችና በተገኙ ውጤቶች ዙሪያ እንዲሁም በሒደቱ በነበሩ ክፍተቶችና በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

የውይይት መድረኩ ለበለጠ ውጤት ግብርናችንን መቅረጽ በሚል መሪ ቃል ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡

በመድረኩ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ የግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሴን፣ የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ በመድረኩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ ኢትዮጵያ 36 ሚሊየን ሄክታር ለእርሻ የሚሆን መሬት እንዳላት አንስተዋል፡፡

ከዚህ ውስጥም በእርሻ የተሸፈነው መሬት 13 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር ብቻ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቷ÷ ተግባርና ውጤት ሳይገናኙ ቀርተው እርዳታ ተቀባይ ሆነን ኖረናል ብለዋል፡፡

እርዳታ በመሰረቱ ከገጠመ አስቸኳይ ችግር ውስጥ ለመወጣት ጊዜያዊ እፎይታ እንደሚሰጥ የታወቀ ቢሆንም÷ ልምዱ  ከቆየ ግን ከተቀባይነት ለመውጣት ያስቸግራል ነው ያሉት፡፡

በምግብ እህል ራሳችንን እስካልቻልን፣ የዜጎችን ህይወት ለማቆየት ምጽዋት ፍለጋ አይኖች እስካማተሩ፣ እጆች እስከተዘረጉ ድረስ ይህ ሁኔታ ከእኛ ጋር የሚቆይ ይሆናል ሲሉም አስረድተዋል፡፡

በምግብ ራሳችንን ከቻልን የምንመገበው ያመረትነውን ከሆነ የህዝባችንን መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት ብቻ ሳይሆን የሀገርን ክብር የምናስጠብቅበት ይሆናል ብለዋል፡፡

የግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ በእያንዳንዱ ዜጋ የሰብዕና ግንባታ ላይ የራሱ አስተዋጽኦ  እንዳለው ጠቅሰው÷የተመጣጠነ ምግብ አግኝቶ ያደገ ዜጋ በአካልም ሆነ በአዕምሮም የጠነከረ እንደሚሆን አውስተዋል፡፡

በየሻምበል ምህረት

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.