Fana: At a Speed of Life!

በጎፋ ዞን ከ155 ሺህ በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ዞኑ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎፋ ዞን ለተከታታይ አራት ዓመታት በአየር መዛባት ምክንያት በተከሰተ የምርት መቀነስ ከ 155 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ መጋለጣቸውን የዞኑ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ወ/ሮ ውብዓለም ዝናቸው÷ በዞኑ ዛላ፣ ዑባ ደብረፀሐይ እና በከፊል ደምባ ጎፋ ወረዳዎች በአየር መዛባትና ምርት መቀነስ ምክንያት 155 ሺህ 248 የቤተሰብ አባላት ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ መጋለጣቸውን ተናግረዋል።

ጽህፈት ቤቱ በዞን ማዕከል በተከፈተ የእርዳታ ማሰባሰቢያ የባንክ አካውንት የተሰበሰበ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ወጪ ሆኖ በአስቸኳይ የእርዳታ እህል ግዥ በመፈፀም ለተጎጂዎች ተጨማሪ እርዳታ እንዲቀርብ ውሳኔ ማስተላለፉንም ገልጸዋል።

የዞኑ መንግሥት የተለያዩ መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሃብቶችና ግለሰቦችን በማስተባበር ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያገኙ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሃላፊዋ የተለያዩ መንግስታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ባለሃብቶችና ግለሰቦች አስካሁን ከሕዝቡ ጎን በመቆም እያደረጉት ላለው ሰብዓዊ ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

ይሁን እንጂ የተደረገው ድጋፍ ከተጎጂዎች ቁጥር አንፃር በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በማቴዎስ ፈለቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.