Fana: At a Speed of Life!

በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን ማስቀጠልና የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን ማሳካት ይገባል – ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እንደ ሀገር በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን ማስቀጠል እና የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን ማሳካት እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በግብርናው ዘርፍ በተደረገ መዋቅራዊ ሽግግር ላይ ያተኮረ “ለበለጠ ውጤት ግብርናችንን መቅረጽ” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን በውይይቱ ላይ ቀደም ሲል ግብርናው የመጣበትን መንገድ፣ በሂደቱ ላይ ያሉ እጥረቶች እና ሙያዊ ርብርብ የሚፈልጉ ጉዳዮችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በገለጻቸውም፥ ባለፉት 20 ዓመታት ግብርናው በፖሊሲ ዝግጅት፣ ስትራቴጂዎችን በማመንጨት፣ በተለይም ጥሩ የገጠር ልማት ፕሮግራም በ2003 ከተቀረጸው ፖሊሲ ጀምሮ በየጊዜው የተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ለዛሬ ዕድገት አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡

ግብርና ተለውጧል የሚባለው፥ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ አመራረት ሳይወሰን፣ ምርታማነቱ በዓይነትና በመጠን ሲጨምር፣ ከገበያ በላይ ትርፍ በማምረት ግብርና ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋጽኦ ሲያበረክት እና ማክሮ ኢኮኖሚውን ሲደግፍ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት ለግብርናው ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው፥ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የመሬት አጠቃቀም፣ የእንስሳት ሃብት ማዘመን፣ ቀጥተኛ የገበያ ትስስርን ማስፋት፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ እና የግብርና ፋይናንስን ማሳደግ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የሰብል ምርታማነትን ካለበት ወደ 70 በመቶ ለማሳደግ መታሰቡን ገልጸው፥ በሰብል የ83 በመቶ፣ በሆርቲካልቸር መስክ እስከ 45 በመቶ እና ቡና 133 በመቶ በማምረት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ወደምትፈልገው ደረጃ እንድትደርስ እነዚህ መመረት አለባቸው ብለዋል፡፡

አማካይ የኢትዮጵያ ምርታማነት ከተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት ቢሻልም፥ ከታይላንድ፣ ቬትናም፣ ቻይና አንጻር ያነሰ በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በቀጣይ፥ በመስኩ ያለውን ዕውቀት በመጠቀም፣ የዘርፉ ባለሙያዎች በንቃት የሚጠበቅባቸውን በማበርከት፣ በዘርፉ ያሉትን ተሳታፊዎች በማሳደግና ሃብት ያላቸውን ወደ መስኩ በማስገባት፣ የፖሊሲና ፕሮግራም ማሻሻያ በማድረግ በትኩረት መሠራት እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

የተገኙ ውጤቶችን ማስቀጠል እና የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን በማሳካት የወተት፣ የሥጋ እና የማር ልማትን ማሳደግ፣ የምርት ጥራት እና የተመጣጣነ ዋጋ እንዲኖር አብዝቶ ማምረት ላይ መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

በዮሐንሰ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.