9ኛው ከፍተኛ የአፍሪካ ሰላምና ፀጥታ ጉባዔ በአልጀሪያ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ አህጉር ሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክረው 9ኛው ከፍተኛ የአፍሪካ ሠላምና ፀጥታ ጉባዔ በአልጀሪያ ኦራን ከተማ እየተካሄደ ነው።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጉባዔው ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
ጉባዔው የአፍሪካ ህብረት የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት እንዲሁም ኤ3 (A3) በመባል የሚታወቀው አፍሪካን በመወከል በተመድ ፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆነው እያገለገሉ ያሉ ሀገራት በምክር ቤቱ የአፍሪካ ሀገራትን ፍላጎትና ጥቅም በብቃት ማስጠበቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየመከረ ነው።
አምባሳደር ብርቱካን በአፍሪካ ለሚያጋጥሙ የሠላምና ፀጥታ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ማበጀት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አይነተኛ መንገድ ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በወቅቱ አፍሪካን በመወከል በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆነው እያገለገሉ ያሉ ሀገራት ኬንያ፣ ጋና እና ጋቦን መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ከፈረንጆቹ ጥር 2023 ጀምሮ ሞዛምቢክ የቆይታ ጊዜዋን የምታጠናቅቀውን ኬንያ በመተካት አባልነቱን ትቀላቀላለች።