Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ቆርጣ ተነስታለች – በፋኦ የአፍሪካ ተወካይ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የግብርና ሥራ ማሳደግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ቆርጣ ተነስታለች ሲሉ በዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የአፍሪካ ተወካይ ዶ/ር አበበ ኃይለገብርዔል ተናገሩ፡፡

ተወካዩ ግብርና ሚኒስቴር“ለበለጠ ውጤት ግብርናችንን መቅረጽ” በሚል መሪ ቃል ባካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር÷አፍሪካ ከአውሮፓ ኅብረት በሁለት እጥፍ የሚልቅ መሬት የምታርስ ቢሆንም አሁንም ግን የምግብ ምርት ከአውሮፓ ታስገባለች ብለዋል፡፡

በርካታ የአፍሪካ ሀገራትም የምግብ እህል ከውጪ በማስገባት ጥገኛ እንደሆኑና በድምሩም ሀገራቱ በዓመት እስከ 56 ቢሊየን ዶላር የሚገመት የምግብ አቅርቦታቸውን ከውጪ በማስገባት እንደሚሸፍኑ አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር አበበ ÷ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ላስመዘገበችው ስኬት የፖለቲካ ምህዳሩ እና የተቋሙ ስኬታማነት ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን አንስተው÷ በዚህም የኢትጵያ መንግስት ሊመሰገን ይገባዋል ብለዋል፡፡

ለአብነትም ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ በተለይም በስንዴ ምርታማነት እና በአረንጓዴ አሻራ ላይ ያስመዘገበችውን ስኬት አንስተዋል፡፡

ይህንን ልምድም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተሞክሮነት ማካፈል አለባት ነው ያሉት፡፡

ድኅነት እና ረሃብ ለሀገር ዘላቂ ዕድገት የመለኪያ መስፈርት ነጥቦች ናቸው ያሉት ተወካዩ÷ድኅነት እና ረሃብ በገጠራማ የአፍሪካ ክፍሎች የሚስተዋል እንደሆነና 55 በመቶ የሚሆነው ሠራተኛ ክፍል በዚሁ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

20 እና 30 በመቶ የሚሆነውን የሀገር ውስጥ የግብርና ምርት የሚሸፍነውም ይኸው የኅብረተሰብ ክፍል እንደሆነም አውስተዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ ላይ የተሰማራው የኅብረተሰብ ክፍል የሚያመርተው ምርት በአማካይ በሌላ ዘርፍ ላይ ከተሰማራው የኅብረተሰብ ክፍል በሦስት እና በአራት እጥፍ ያነሰ ነውም ብለዋል ዶ/ር አበበ፡፡

ይህ የሚያሳየው ከግብርናው ዘርፍ ውጪ የተሰማራው የኅብረተሰብ ክፍል ምርታማ መሆኑን ሳይሆን በግብርናው ዘርፍ ላይ የሚሰራው የኅብረተሰብ ክፍል እጅግ በጣም አነስተኛ መሆኑን እና ምርታማነታችንም ዝቅተኛ መሆኑን ነውም ብለዋል፡፡

በአለማየሁ ገረመው

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.