Fana: At a Speed of Life!

ኅብረ ብሔራዊነታችን የአይበገሬነታችን ምንጭ ነው- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኅብረ ብሔራዊነታችን የአይበገሬነታችን ምንጭ ነው ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡
 
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓልን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡
 
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል ፡-
 
ኅብረ ብሔራዊነታችን የአይበገሬነታችን ምንጭ ነው
 
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከአፈጣጠሯም ኅብረ ብሔራዊት ሀገር ናት፡፡ ከጥንት ጀምሮ የብዝኃ ባህል፣ ቋንቋና ማንነት ባለቤት የሆኑ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተጋምደውና ተሰናስለው የሚኖሩባት ታላቅ ሀገር ናት፡፡ ይህ ኅብረ ብሔራዊነቷና የብዝኃ ብሔር ሀገር መሆኗ በአንድ አንድ ወገኖች እንደ ሥጋትና አለመታደል ሲቆጠር ይስተዋላል፡፡
 
በተለያዩ ጊዜያት ወጥ ማንነትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግሥትን ለመገንባት ታስቦ ተሞክሯል፡፡በሌላ በኩል ብዝኃነታችን የውበታችንና የታላቅነታችን ምንጭ፣ የኩራትና የክብራችን መነሻ መሆኑ ያልታያቸው ደግሞ የተነጣጠለና የሚቃረን ማንነትን ለመፍጠር ብዙ ለፍተዋል፡፡
 
ብዝኃነትና አብሮነትን እንደ ጸጋ እና የጥንካሬ ምንጭ ከመውሰድ ይልቅ እንደ ዕዳ በመቁጠር በልዩነት መገለጫዎቻችን ብቻ በመታጠር የተነጣጠለ ማንነትን ለመፍጠር ተሠርቷል፡፡ከታሪካችን የምንማረው ግን ብዘኃነታችን የሥጋት ምንጭም፣ ዕዳም አለመሆኑን ነዉ፡፡
 
ዛሬ ላይ ቅኝ ያልተገዛን ሕዝቦች ነን ብለን አንገታችንን ቀና አድርገን የምንናገረው፣ ሉዓላዊነቷ ተጠብቀው የቆየ ሀገር አለን የምንለው፣ የቅርብና የሩቅ ጠላቶቻችን በተለያዩ ወቅቶች ሊደፍሩን ሲሞክሩ ያልቻሉን ከሁሉም በላይ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ውስጥ የተፈጠረ ዕሴት ስላለን ነው፡፡
 
ለዚህም ነው ኅብረ ብሔራዊነታችን የአይበገሬነታችን ምንጭ ነው የምንለዉ፡፡ የዘንድሮው 17ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን አከባበር መሪ ቃልም የሚያስረዳን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የሠላማችን ምሶሶም ጭምር መሆኑን ነዉ፡፡
ዕለቱ ለብዘኃነታችንና ኅብረ ብሔራዊነታችን ዕውቅና የሰጠው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት የጸደቀበት ቀንንለማሰብ ነው፡፡ዘንድሮው ዕለቱን የሚናከብረዉ ሀገራችን የተደቀነባት የህልውና አደጋ በልጆቿ የጋራመሥዋዕትነት ቀልብሳ ወደ ሰላማዊ ጎዳና እየተንደረደረች ባለችበት ወቅት ነው፡፡
 
ሀገራችንን ከመበተን አደጋ በመታደግ የኢትዮጵያዊያን አይበገሬነት በተረጋገጠበት ዓመት ይህ በዓል መከበሩ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕብረብሔራዊ አንድነት እሳቤ እየተመራ ዘላቂ ጥቅሙን እያረጋገጠ እንደሚገኝ የሚያሳይ ነዉ፡፡
 
በዚህ ዓመት በዓሉን ስናከብር ከዚህ ቀደም እንደነበረው የልዩነት ትርክቶችን ብቻ እየዘመርን ሳይሆን፤ ብዝኃነታችን ለአንድነታችን፤ አንድነታችንም ለብዝኃነታችን ምሦሦ የሚሆኑበትን ሁኔታ እያመቻቸን
ሊሆን ይገባል፡፡ በዓሉን የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች አንድም ብዙም መሆናቸውን እያሰብን ልናከብረው እንደሚገባ መንግሥት መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡
 
ሀገራችን ኢትዮጵያ እጅግ ያማሩ እና የዳበሩ ቋንቋዎች፤ ቱባ ባህሎች፤ ሃይማኖቶች፤ ታሪኮች እና እሴቶች ባለቤት የሆነች ሀብታም ሀገር ናት፡፡ እነዚህ ብዝኃነታችንን ያደመቁ የሀገራችን መለያ እሴቶች በማወቅ፤ በማክበር እና በማሳደግ ለሀገራዊ አንድነታችን ግብዐት ማድረግ እንጂ በምንም መልኩየግጭት መንስዔ ልናደርጋቸው አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ዕሴቶችም መጋመድን እንጂ መለያየትን አያበረታቱም፡፡
 
በመሆኑም፤ ሀገራችን ብዝኃነት የተከበረባት እና አንድነቷ የጸና እንዲሆን የሚደረጉ ጥረቶችን በሚያግዝ መልኩ ይህንን ዓመታዊ በዓል ማክበር ይጠበቅብናል፡፡
 
በመሪ ቃሉ ላይ በግልጽ እንደሰፈረውም፤ ሕብረብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን ዋስትና መሆኑን የዘንድሮውን በዓል ስናከብር በተጨማሪነት ማሰብ ያለብን ጉዳይ ነው፡፡ ብዝኃነትን የሚያጠፋም ሆነ አንድነትን የሚንድ ሁኔታ በኢትዮጵያ ምድር ዘላቂ ሰላምን ሊያመጣ እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
 
በኢትዮጵያ የሚከናወን የሰላም ግንባታ ሂደት ብዘኃነትን ከአንድነት ጋር ካላዋደደ ጠቃሚ ፍሬ ሊያፈራ አይችልምና፡፡
 
መንግሥት በሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን እንዲሆን ብዝኃነትን እና አንድነትን የሚያስማማ መንገድ በመከተል ዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ለመገንባት ከምንጊዜውም በላይ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረውን ጦርነት በሰላማዊ አማራጮች መቋጨት ያስፈለገውም ይህንን መርሕ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡
 
አሁንም ቢሆን በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በጽንፈኛ አሸባሪ ኃይሎች የሚደረገው ጥቃት መንግሥት የጀመረውን የዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት ለማደናቀፍ እንዲሁም ሕዝባችንን በሀገሩ ላይ ተስፋ ለማስቆረጥ የታለመ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
 
ሀገራችንን ለመበታተን የሚደረጉ አፍራሽ የጽንፈኛ አሸባሪዎችን ትንኮሳዎች በኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን አክሽፈን ዘላቂ ሰላማችንን ለመገንባት ሁላችን የበኩላችንን ሚና እንድንወጣ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል፡፡
 
በዓሉ እዉነተኛ ህብረ ብሔራዊአንድነታችን ጎልቶ የሚታይበትና የሀገራችን ሠላም ይበልጥ የሚረጋገጥበት እንዲሆን መንግሥት ይመኛል፡፡
 
“ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም”
 
ኅዳር 28/ 2015 ዓ/ም
 
አዲስ አበባ
 
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.