Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል የድንገተኛ ሕክምና ምላሽና ጤና ተቋማትን አገልግሎት የማስጀመር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስቴር በትግራይ ክልል የድንገተኛ ሕክምና ምላሽ እና ጤና ተቋማትን አገልግሎት የማስጀመር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገለጸ፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የሕክምና አገልግሎት ለሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሰብዓዊ ዕርዳታ፣ የሕይወት አድን ሕክምና የሥርዓተ ምግብ እንዲሁም የጤና አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ ሥራ በጤና ሚኒስቴር እና አጋር ድርጅቶች እየተከናወነ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

መድኃኒቶችና የሕክምና ግብዓቶችን ማድረስ በተመለከተ÷ ከጎንደር መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ወደ ሽረ ቅርንጫፍ 13 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ሕይወት አድን መድኃኒቶችና የሕክምና ግብዓትቶችን በተለያዩ ዙሮች ለሽረና በአቅራቢያው ለሚገኙ ከተሞች ማድረስ መቻሉ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ከደሴ ቅርንጫፍ ወደ አላማጣ እና አካባቢው ላሉ ጤና ተቋማትም 20 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚያወጡ ሕይወት አድን መድኃኒቶችና የሕክምና ግብዓትቶችን ማድረስ ተችሏል ነው የተባለው፡፡

የጸረ-ወባ፣ የስኳር፣ የኩላሊት እጥበት ፣ የፀረ-ቲቢ፣ ጸረ-ደም ግፊት፣ ለሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎት እና ለመሳሰሉት የሚውሉ 78 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ዋጋ ያላቸው ሌሎች ሕይወት አድን መድኃኒቶችም÷ በዓለም ጤና ድርጅት እና በዓለምአቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በኩል ወደ መቀሌ ማድረስ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡

በቀጣይም ተጨማሪ የሕይወት አድን ሕክምና ግብዓቶችን ለማድረስ በሂደት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የመቀሌ እና የሽረ ቅርንጫፎች በተገቢው መንገድ የሕይወት አድን መድኃኒቶች እና የሕክምና ግብዓቶችን እየተቀበሉና እያሰራጩ ይገኛሉ ነው ያለው ሚኒስቴሩ።

የጤና አገልግሎት ትግበራን በተመለከተም የሕክምና አገልግሎት ለማስጀመር እና የመስክ ምልከታ ለማድረግ ከጤና ሚኒስቴርና ከተለያዩ ሆስፒታሎች የተውጣጡ ባለሙያዎችን ወደ ሽረ፣ አክሱም እና ዓድዋ ከተሞች ተልከዋል ተብሏል፡፡

በሽረ፣ አክሱም እና ዓድዋ ሆስፒታል እንዲሁም በአቅረቢያው ባሉ ጤና ጣቢያዎች የመስክ ምልከታ ተደርጓል፡፡

በሽረ ስሁል ሆስፒታል ከጦርነቱ በፊት ከነበሩ 520 ሠራተኞች ውስጥ 411 ወደ ሥራ ለመመለስ ሪፖርት ማድረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡

ሆስፒታሎቹ የተመላላሽ፣ የተኝቶ ማከሚያ፣ የድንገተኛ፣ እንዲሁም የቤተ ሙከራ እና የፋርማሲ አገልግሎት መስጫ እንደነበሩና የተላኩትን ግብዓቶች በመጠቀምም የታለመላቸውን አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተመላክቷል፡፡

ጤና ተቋማቱን ሥራ ለማስጀመር እና በሰው ኃይል ለማደራጀትም በሦስት ሆስፒታሎች ማለትም በሽረ፣ በአክሱም እና በዓድዋ እንዲሁም በዙሪያቸው ባሉ 15 ጤና ጣቢያዎች ላይ ወደ ሥራ ለተመለሱ ባለሙያዎች ክፍያ የሚውል ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረስ ወደ ቦታው የፋይናንስ እና የሰው ሐብት ባለሙያዎች መላካቸው ተነስቷል፡፡

በሽረ ላሉ የጤና ባለሙያዎች ክፍያ መክፈል መጀመሩም ነው የተገለጸው፡፡

በግጭቱ የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ የማደራጀት ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.