Fana: At a Speed of Life!

የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት የኢትዮጵያን የበረራ ደኅንነት አጠባበቅ አደነቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት አስተዳደር ምክትል ረዳት ኃላፊ ካሪግ ሊየንስ የኢትዮጵያን የበረራ ደኅንነት አጠባበቅ አደነቁ፡፡

ካሪግ ሊየንስ እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ ከበረራ ደኅንነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ምክክር አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ካሪግ ሊየንስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚሰጠው አገልግሎት በአፍሪካም ሆነ በዓለምአቀፍ ደረጃ መልካም ስም ያለው መሆኑን ጠቁመው ይህ ውጤት በበረራ ደኅንነት ዘርፍ የተሠሩ ሥራዎችና የተገነቡ አቅሞች ጭምር ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከበረራ ደኅንት ጋር በተያያዘ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በአደረጃጀት ጠንካራ መሰረት መጣሉን ተረድቻለሁ ማለታቸውን ተገንዝቤያለው ማለታቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የላከልን መረጃ ያመለክታል፡፡

አሜሪካ የበረራ ደኅንነትን በማረጋገጥ ረገድ በቴክኒክ፣ በሎጀስቲክስ፣ በቴክኖሎጂና በሥልጠና መስኮች ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ እንዲሁም በጋራ የሚሠሩ ሥራዎችን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ እንደገለጹት÷ ውስብስብ የደኅንነት ሥጋቶች በተደቀኑበት የአቪዬሽን ዘርፍ ውጤታማ ለመሆንና የኢትዮጵያን አየር መንገድ መልካም ስም ለማስቀጠል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የበረራ ደኅንነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች የማሟላት፣ የሰው ኃይል አቅም የመገንባትና የአደረጃጀት ክለሳዎች በመከናወናቸው ሥጋቶችን መቀነስ ተችሏል ብለዋል፡፡

ከውይይቱ ባሻገር ካሪግ ሊየንስ የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱን ዲጂታል ኤግዚቢሽን ጎብኝተዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.