Fana: At a Speed of Life!

የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ነገ ለሚከበረው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ17ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፈ፡፡
17ኛውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ስናከብር ኅብረ-ብሔራዊ መግባባትንና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩና የሚያዘልቁ ሁነቶችንና ተግባራት በማከናወን ሊሆን ይገባል ብሏል ምክር ቤቱ በመልዕክቱ፡፡
ምክር ቤቱ በመልካም ምኞት መልዕክቱ÷ ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ ባህልና ስነ-ልቦና የምንጋራ የብዝሃነትና የኅብረ-ብሔራዊ አንድነት መገለጫና ተምሳሌት የሆንን የትልቅ ሀገር ሕዝቦች ነን ብሏል፡፡
ምንም እንኳ በየጊዜው የሚያጋጥሙን የውስጥና የውጭ ተግዳሮቶች ውስብስብ ቢሆኑም÷ እጅ ሳንሰጥና ለጥፋት ኃይሎች ወጥመድ ሰለባ ሳንሆን በብሔራዊ አንድታችን የተባበረ ክንድ መክተን የሀገር አንድነትን ያዘለቅን ሕዝቦች ነን ብሏል ምክር ቤቱ፡፡
በመሆኑም ይህንን ልናፀና፤ ልማታችንን ልናፋጥንና ሰላማችንን ልንጠብቅ ይገባል ነው ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፡፡
ለዚህም ኢትዮጵያውያን እና በየደረጃው ያለ የሚመለከተው አካል ለሕዝቦች ዘላቂ ሰላም፣ ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር እና ለኢትዮጵያ ብልጽግና የበኩሉን የመወጣት ኃላፊነት እንዳለበትም ተመላክቷል፡፡
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሀገራችን ያሉ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ፣ ብሔራዊ መግባባት፣ መቀራረብና መደማመጥ እንዲፈጠር አስቻይ የታሪክ ምዕራፍ እንደሚፈጠር ይጠበቃል ያለው ምክር ቤቱ÷ ለውጤታማነቱም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ሐሳብ ለ17ኛ ጊዜ ነገ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሐዋሳ ከተማ ይከበራል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.