Fana: At a Speed of Life!

ለሰላም ስምምነቱ ትግበራ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስትና ህወሓት መካከል ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ትግበራ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተናገሩ፡፡

እንዲሁም አሸባሪው የሸኔ ቡድን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያዩ ጥቃቶችን እየፈፀመ እንደሚገኝ የገለጹት አባላቱ÷ መንግስት ሰላማዊ አማራጭን ሲከተል ቢቆይም ሕግን ለማስከበር እንደሚገደድ ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ዘላቂነት ባለው መንገድ ለመፍታት እንደሚሠራም አሳውቀዋል፡፡

ለአራት ቀናት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የመከረው የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ተጠናቋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አቅምን በውጤት ፈተናን በስኬት በሚል መሪ መልዕክት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ÷ በተለያዩ ሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው ቀዳሚ አጀንዳው ካደረጋቸው ጉዳዮች መካከል የአገሪቱ ሰላም አንደኛው ነው።

በተለይም ከህወሓት ጋር የተደረሰው የሰላም ስምምነት የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያመላከተ በመሆኑ÷ ለስምምነቱ ትግበራ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አቋም መያዙን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ ተናግረዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ ለአገረ መንግስት ግንባታው ፋይዳው የላቀ መሆኑንም አንስተዋል።

መንግስት በመላው ኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ያነሱት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ÷ አሸባሪው የሸኔ ቡድን ግን ዛሬም በእኩይ ተግባሩ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

ቡድኑ የመላው ኢትዮጵያውያን ጠላት በመሆኑ በጋራ በመሆን መመከት እንደሚገባ እና ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንደሚያስፈልግ አባላቱ ተናግረዋል።

መንግስት የትኛውም ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ቁርጠኛ አቋም አለው ያሉት አባላቱ÷ ከሰላማዊ መንገድ ውጪ የሚደረጉ የትኛውም አማራጮች አክሳሪ መሆናቸውን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.