Fana: At a Speed of Life!

የጋራ ቤታችንን በጋራ እንጠብቅ – አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ድኅነትን ታሪክ ለማድረግ በጋራ ርብርብ እያደረግን የሁላችንንም ቤት ኢትዮጵያን በጋራ እንጠብቅ ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ጥሪ አቀረቡ፡፡

አቶ ደስታ በ17ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የዘንድሮው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓልን ልዩ የሚያደርገው ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጠሩ የእርስ በርስ ግጭቶችን በውይይት ለመፍታት መስማማት ላይ በተደረሰበት ማግስት በመከበሩ ነው ብለዋል፡፡

እንደኢትዮጵያ ብዝኃ ባህል፣ ብሔር እና ሐይማኖት ላላቸው ሀገራት ኅብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ተመራጭ የመንግሥት አወቃቀር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም ሁሉም አካባቢዎች ራሳቸውን እንዲያደራጁ እና እንዲያለሙ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት፡፡

መንግሥት ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ሁሉንም ያማከለ ፌደራሊዝም እየገነባ ለመሆኑ እኛ ሕያው ምስክሮች ነን ብለዋል፡፡

ሁሉም ማንነቶች ሊከበሩና ሊጠበቁ የሚችሉት ሀገርና ሕዝብ እስካለ ድረስ መሆኑን ጠቁመው፥ “የኢትዮጵያ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች በጋራ አብረን በመኖር የጋራ ዕሴት የገነባን መሆናችንን አውቀን አንድነታችንን አጠናክረን ብዙዎች የሚጓጉላትን ኢትዮጵያችንን በጋራ እንጠብቃት፤ በጋራ እንገንባት” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ድኅነትን ታሪክ ለማድረግ በጋራ ርብርብ እያደረግን የሁላችንንም ቤት ኢትዮጵያን በጋራ እንጠብቃት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ክልሉ የቆየውን የአብሮነት ዕሴቱን በመጠቀም ሁሉም በእኩልነት የሚኖርበት እንዲሆን መሠራቱንም ጠቁመዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.