Fana: At a Speed of Life!

ብዝሃነትን ያከበረ የፌዴራል ስርዓት ለመገንባት በተቀናጀ መልኩ የተጀመረውን ስራ ማጠናከር ይገባል- አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ብዝሃነትን ያከበረ የፌዴራል ስርዓት ለመገንባት በተቀናጀ መልኩ የተጀመረውን ስራ ማጠናከር እንደሚገባ የፌዴሬሽም ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።

አቶ አገኘሁ ተሻገር በ17ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ቀኑ ሲከበር አላማው የህዝቦችን አንድነት ለማጠናከር እንዲሁም አሁን ያለውን እና ወደፊት የሚተካውን ትውልድ አንድነትና ትስስር ለማጎልበትና በህዝቦች መካከል ትውውቅ መፍጠር እንዲቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት እነዚህን አላማዎች ለማሳካት ባለፉት አመታት በተለያዩ ክልሎች በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች እንዲከበር ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ በህብረ ቀለማት ያሸበረቀች፣ የባለብዙ ማንነት ለመሆኗ ማረጋገጫም ሆኗታል ነው ያሉት።

የየብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶችም አሁን ላይ እየተሰሩ ለሚገኙ የኪነ ጥበብ ውጤቶች ማጌጫዎች መሆን መቻላቸውን አንስተዋል፡፡

በዓሉ  ሲከበር  በህዝቦች ዘንድ መቀራረብና መተማመንን የመፍጠር አቅም  እንዳለው የገለጹት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሸገር፥ አንድነታችንን ማጠናከርም ይገባናል ብለዋል፡፡

ምሁራን፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የሀገር ሽማግሌዎች የሕግ የበላይነት እንዲከበርና ወንድማማችነት እንዲጎለብት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚበገባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የጋራ ቤታችንን  በጽኑ አለት ላይ ለማቆም አንድነቷ ምሰሶ፣ ብዝሀነቷ ደግሞ ለአንድነቷ ደጋፊ ወጋግራዎች ሆነው አገልግለዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በሻምበል ምህረት እና በብርሀኑ በጋሻው

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.