Fana: At a Speed of Life!

በተናጠል ጎልተን ለመታየት ሳይሆን በጋራ ለማበብ ልባችን የቀና አዕምሯችን የሚያስተውል ሊሆን ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተናጠል ጎልተን ለመታየት ሳይሆን በጋራ ለማበብ ልባችን የቀና አዕምሯችን የሚያስተውል ሊሆን ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሀዋሳ እየተከበረ በሚገኘው 17ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር ላይ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክተ አስተላልፈዋል፡፡
 
በመልዕክታቸውም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል፣ ኢትዮጵያ በድምቀት እና በሙላት የምትታይበት የኢትዮጵያዊነት ምልክት እና ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ የሁላችንም ቤት ናት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በጋራ የምናድግበትንና የምንበለጽግበትን ሁኔታ በጋራ መፍጠር ካልቻልን ማናችንም በሰላም መኖር እና ወጥተን መግባት አንችልም ብለዋል፡፡
 
የእያንዳንዳችን ችግር ሊፈታ የሚችለው የሁላችንም ችግር ሲፈታ ነው፣ በተናጠል የራሱን ችግር ብቻ መፍታት የሚችል ማንኛውም ግለሰብ እና ቡድን ከኢትዮጵያ ችግር በፊት ቀድሞ የሚፈታ የሰፈር ችግር እንደሌለ መገንዘብ አለበት ነው ያሉት፡፡
 
በዚህ ቀን የሁላችን ባህል፣ ታሪክ ቅርስ፣ እሴት፣ የኢትዮጵያ ሃብት እና የጋራ ኩራት ሆኖ የሚታይበት፣ ሁላችንም ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ መሆናችን እና ውበታችን በኢትዮጵያ ጥላ ስር ጎልቶ የሚታይ እና የምንማርበት ዕለት ነው ሲሉም አውስተዋል፡፡
 
ሀገር በቤት ይመሰላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ማገሩ፣ ወራጁ፣ ጣራው ተሰናስለው ቤት እንደሚሆኑ ሁሉ ሁሉም ብሔሮች እና ብሄረሰቦች እያንዳንዳቸው ሰበዝ ሆነው ሲደመሩ ታላቋን እና ውቧን ኢትዮጵያ ያሳያሉ ብለዋል፡፡
 
ስለሆነም በተናጠል ጎልተን ለመታየት ሳይሆን በጋራ ለማበብ ልባችን የቀና አዕምሯችንም የሚያስተውል እና የሚያሰላስል ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
 
ትናትን ያለፈ እና ያመለጠ ታሪክ ነው፣ ትናትን ለመማሪያ ብቻ መጠቀም ከቻልን ነጋችን ያማረ ይሆናል፤ ዛሬ የትናትን ጉዳይ እያነሳን ብንወቅስና ብናወድስ ሰዎቹ የሉምና አይሰሙንም ትርጉምም የለውም ብለዋል፡፡
 
እኛ መልካም ነገን ለልጆቻን ለመገንባት ከትናንት መማር አለብን፤ መጪው ትውልድ ከልመና የተላለቀ እና የተማረ እንዲሆን መገፋፋቱን እና መጠላላቱን መተው ይገባል ነው ያሉት፡፡
 
በኢትዮጵያ ውስጥ ከግራ ከቀኝ ዋልታ የረገጡ እሳቤዎች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ለብነትም ከትናንት እሳቤ ያልተላቀቁ፣ ነገ የሚሰራበትን እያንዳንዱን ብሎኬት የሚያፈርሱ፤ በጋራ መኖር ሳይሆን መገፋፋትን የሚመርጡ፣ በሌሎች አጀንዳ የተገዙ፣ በንጹሃን ደም ፖለቲካ የሚሰሩ ጥቂት ግለሰቦች እና ቡድኖች እንዲሁም የሚዲያ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
 
“ለእነዚህ ጊዜውን ለሳቱ ወንድሞቻችንን ያለኝ ምክር ዛሬም ኢትዮጵያ ትፈተናለች እንጂ አትፈርስም የሚል ነው” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብልጽግና እና ልዕልና የሚመነጨው ከእውነት እና ፍቅር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በአንጻሩ የተሸናፊ ሃይሎች ጀንዳ ጥላቻ፣ ግድያ እና መገፋፋት ንጹሃንን ማጎሳቆል እንደሆነ ጠቁመዋል።
 
ከግራም ከቀኝም ያሉ ዋልታ የረገጡ እሳቤዎችን ለኢትዮጵያ ስለማይበጁ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአጀንዳዎቹ ጀሮ መስጠት የለበትም ሲሉም አሳስበዋል፡፡
 
በሰሜን ኢትዮጵያ የጀመርነው ሰላም ዘላቂ አስተማማኝ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነውም ብለዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.