Fana: At a Speed of Life!

ሕግ የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በፀጥታ ኃይሉ መስዋዕትነት እና በሕዝቡ ቀና ተባባሪነት እየሰከነ የመጣው ሰላማችንን ወደ ኋላ ለመመለስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለመቆጣጠር የሚያከናወነው ሕግ የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ሰሞኑን በአዲስ አበባ በነበረው ችግር ምክንያት ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው 97 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል፡፡

በሕዝብ ፍላጎትና በመንግስት ቁርጠኝነት የተጀመሩ የሰላምና የፀረ ሌብነት ትግሉን ለማደናቀፍ የማይተኙ ጠላቶች መልካቸውን ቀይረው መከሰታቸውን ህብረተሰቡ እንዲገነዘብ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቋል፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የኦሮሞ ባህል ተጭኖብናል እና የኦሮሞ ሕዝብ እየሞተ ነው የሚል እርስበእርሱ የሚቃረን አጀንዳ በመፍጠር እንዲሁም የወልቃይትና የአዲስ አበባ ጉዳይ አንድ ነው የሚል መፈክር ይዘው በመውጣት የኢትዮጵያን እና የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ ከሰንደቁ ላይ በማውረድ መሬት ላይ የጎተቱ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ሰሞኑን በአንዳንድ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የጥፋት አጀንዳቸውን ከተቀበሉ ጥቂት መምህራንና ተማሪዎች ጋር በመሆን ምንም የማያውቁ ተማሪዎችን ከፊት በማሰለፍ ባስነሱት ረብሻ በትምህርት ቤቶች ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው በኩል የፀጥታ ኃይሉ ሕጋዊ ተግባሩን እንዳይወጣ ለማሸማቀቅ ታስቦ ከዚህ በፊት የተቀረፁ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምስሎችን አሁን እንደተፈፀመ በማስመሰልና በማሰራጨት ህብረተሰቡ ለአመፅና ብጥብጥ እንዲተባበር እያነሳሱ መሆኑንም ፖሊስ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸውን 97 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል፡፡

የፀጥታ ኃይሉ በሀሰተኛ ሚዲያዎች ሳይሸማቀቅ ከሕዝብና ከመንግስት የተሰጠውን አደራ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስታውቆ÷ አጥፊ ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦች ከእኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል፡፡

የአዲስ አበባ የወትሮ ሰላምና የነዋሪዎቿ በሰላም ወጥቶ መግባት የሚያንገበግባቸው ግለሰቦችን በመለየት ሕግ የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቀው ፖሊስ÷ ህብረተሰቡም ልጆቹን ከመምከር ባሻገር የሰላሙ ፀር የሆኑ ግለሰቦችን አጋልጦ ለፀጥታ አካላት በመስጠት የዘወትር ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡

የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትና መረጃዎችን ለመስጠትም በ 011-1-11-01-11 እና በነፃ የስልክ መስመር 991 ላይ በመደወል መረጃ መስጠት እንደሚቻል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.