Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ቀይ መስቀል ማኅበሮች የደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እና ሩሲያ ቀይ መስቀል ማኅበር የደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የሚያስችል ውይይት አድርገዋል።

የሩሲያ ቀይ መስቀል ማኅበር እና የጤና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርን እና የደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታልን ለመደገፍ ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ ነው ውይይቱ የተካሔደው፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ፕሬዚዳንት አበራ ቶላ እና የሩሲያ ቀይ መስቀል ማኅበር ፕሬዚዳንት ፓቭል ሳቭቹክ በስምምነቱ ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

ዶክተር ፓቭል ሳቭቹክ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ የደጃዝማች ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ከሩሲያ 15 ዶክተሮችን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት አገልግሎት እንዲሰጡ እና ለሆስፒታሉ የሕክምና ባለሙያዎች ልምድ እንዲያካፍሉ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡

አቶ አበራ ቶላ የሩሲያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ በመሥራት የረጅም ዓመት ልምድ ያለው መሆኑን ገልጸው÷ በተለይም የባልቻ ሆስፒታልን በተለያዩ መንገዶች ሲደግፍ ቆይቷል ብለዋል።

በቀጣይ የመድኃኒት፣ የአምቡላንስ ድጋፍ እና የሕክምና ባለሙያዎቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ፓቭል ሳቭቹክ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እና ለደጃዝማች ሆስፒታል በቀጣይ የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.