Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማሳደግ ተስማሙ

 

አዲስ አበባ፣ህዳር 29፣2015 (ኤፍ ቢሲ) ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማሳደግ ተስማሙ።

በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የሁለቱ ሀገራት የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ተጠናቋል።

በመዝጊያው ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ፥ የጋራ ስብሰባው በወዳጅነት መንፈስ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ማሳደግ በሚቻልበት መንገድ ውጤታማ ሆኖ መካሄዱን ጠቁመዋል።

ስብሰባው የሁለቱን ሀገራት ባለብዙ ዘርፍ ግንኙነት ማሳደግ የሚቻልባቸውን መልካም አጋጣሚዎች ለመመልከት እንዲሁም የተደረሱ ስምምነቶች እና የተገቡ ቃሎች አፈፃፀም የሚገኙበትን ደረጃ ለማየት ማስቻሉን ነው ያመለከቱት።

የሩሲያ ፌዴሬሽን ልዑክ መሪ ኢቬግኒ ፔትሮቭ በበኩላቸው፥ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት 300 ዓመታት መሻገሩን አውስተዋል።

ይህ ግንኙነት መከባበር እና የጋራ ተጠቃሚነትንም መሰረት ያደረገ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ለሶስት ቀናት የተካሄደው የኢትዮ-ሩሲያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በማዕድን፣ ሀይል፣ ንግድ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ እና በቱሪዝም መስኮች መተባበር በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ መክሯል።

ቀጣዩን የኮሚሽኑን ስብሰባ በአውሮፓውያኑ 2024 ላይ በሩሲያ እንዲካሄድም ከስምምነት መደረሱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.