Fana: At a Speed of Life!

ሴቶች በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ማንኛውንም ሚና መጫወት ይችላሉ – ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ የተመራ ልዑክ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በዱባይ በሚካሔደው “ቢግ 5” የግንባታ የንግድ ትርዒት እየተሳተፈ ነው፡፡

ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በመድረኩ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ የኢትዮጵያ መንግሥት ሴቶችን ወደ ከፍተኛ አመራርነት በማምጣት ሀገራቸው የምትጠብቅባቸውን እንዲወጡ ዕድል እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

ሴቶች በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ማንኛውንም ሚና መጫወት እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡

በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ብዝሃነትን ማስተዋወቅና ለሴቶች ተጨማሪ እድሎችን ከመስጠት ባለፈ በርካታ ሴቶችን ወደ አመራርነት በማሳደግ መጪው ትውልድ ፈለጋቸውን እንዲከተል ለማነሳሳት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ሴት ባለሙያዎች አቅማችውን ለዓለም እንዲያሳዩ ያበረታቱን ወይዘሮ ጫልቱ÷ አብረን ጠንክረን በመቆም ቀጣዩ ትውልድ ሊመለከታቸው የሚገቡ አርዓያዎች መሆን አለብን ነው ያሉት፡፡

ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ ማቅረባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

“ቢግ 5” የግንባታ የንግድ ትርዒት በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ እና በደቡብ እስያ ትልቁ እና ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለው የግንባታ ትርዒት ሲሆን÷ ከዚሁ ጎን ለጎን በግንባታው ዘርፍ ያሉ ሴቶችን የሚያስተዋውቅ መድረክ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.