Fana: At a Speed of Life!

ከሑመራ ማከፋፈያ ጣቢያ የሚገኘው የመካከለኛና የዝቅተኛ መስመር ጥገና ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሑመራ ማከፋፈያ ጣቢያ ኤሌክትሪክ የሚያገኙት ሑመራ፣ ዳንሻ፣ ባዕኸር፣ ማይካድራ፣ ዓብደራፊዕ፣ አብርሃጅራ፣ ሶሮቃ፣ ዓዲጎሹ፣ ዓዲረመፅ ከተሞችና እና በርካታ ቀበሌዎች ላይ የሚገኘው የመካከለኛና የዝቅተኛ መስመር ጥገና መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

የሽረ፣ ሑመራ፣ ወልቃይትና አካባቢዎቻቸው የመካከለኛና ዝቅተኛ መስመር ጥገና ሥራ ቀደም ብሎ ስለተጠናቀቀ÷ ከተከዜ የተዘረጋው ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ ጥገና ተከናውኖ ትናንት ምሽት ላይ ተቋርጦ የነበረው አገልግሎት መልሶ ለማገናኘት ሙከራ መደረጉ ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጅ በከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ ትራንስሚሽን መስመሩ ላይ ያጋጠመው ብልሽት ሙሉ ለሙሉ ባለመቀረፉ አካባቢዎቹ ምሽቱን ለማገናኘት አለመቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡

ለሽረ ከተማ የሚሰጠው የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ ትራንስሚሽን መስመርም ብልሽት ስላጋጠመው ማምሻውን ዳግም አገልግሎቱን ያገኘችው ሽረ ከተማም ኃይል እንደተቋረጠባት ተገልጿል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጥገና ሥራውን በአፋጣኝ እንዲያጠናቅቅ በጋራ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

ጥገናው እንደተጠናቀቀ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ዳግም እንደሚጀመር በመገንዘብ የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች በትዕግስት እንዲጠብቁ አገልግሎቱ ጠይቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.