Fana: At a Speed of Life!

ከ55 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከፍተኛ ጥገና የተደረገለት የአላውኃ ድልድይ ነገ ለትራፊክ ክፍት ይሆናል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ከ55 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከፍተኛ ጥገና የተደረገለት ወልዲያን ከቆቦ የሚያገናኘው የአላውኃ ድልድይ ነገ ለትራፊክ ክፍት እንደሚሆን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ፡፡

ድልድዩ በግጭት እና ጎርፍ ምክንያት ጉዳት ደርሶበት እንደነበር ተገልጿል፡፡

በአስተዳደሩ የድልድይ እና ስትራክቸር ሥራዎች ዳይሬክተር ኢንጂነር ጌትነት ዘለቀ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ድልድዩን ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ሁለት ወር ከሁለት ቀን ጊዜ ወስዷል፡፡

109 ነጥብ 7 ሜትር ርዝመት እና 4 ነጥብ 2 ሜትር ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ እንዲሁም አዲስ ተገጣጣሚ የብረት ድልድይ እና ድልድዩን የሚሸከም አንድ ምሰሶ እንደ አዲስ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡

ይህ ግንባታ አንድ ተሽከርካሪ እንዲያሳልፍ ተደርጎ ለጊዜው የተሠጠ መፍትሔ መሆኑን ጠቁመው÷ ድልድዩን በቋሚነት ለመገንባት ዕቅድ መያዙን አመላክተዋል፡፡

የግንባታ ሥራው ዛሬ በመጠናቀቁ ከነገ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ለትራፊክ አገልግሎት ክፍት እንደሚሆንም አረጋግጠዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.